Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቤተ መቅደሱ ቅዳሴ 1 ከዚህም በኋላ የቄሌ-ሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና፥ ሳትራቡዛኒስ፥ ባልንጀሮቻቸውም ንጉሡ ዳርዮስ እንዳዘዘ ይሠሩ ዘንድ ጀመሩ። 2 እነርሱም ተግተው ከአይሁድ ሽማግሌዎች ጋር ቆመው ያዝዙ ነበር። 3 የቤተ መቅደሱም ሥራ፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ ትንቢት እየተናገሩላቸው ፈጥኖ ተከናወነ። 4 በፋርስ ነገሥታት በቂሮስና ዳርዮስ፥ በአርጤክስስም ፈቃድ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሥራውን ፈጸሙ። 5 ቤተ መቅደሱ አዳር በሚባል ወር በጨረቃ በስምንተኛው ቀን በዳርዮስ በስድስተኛው ዓመተ መንግሥት ተፈጸመ። 6 የእስራኤል ልጆችና ካህናት፥ ሌዋውያንም፥ ከምርኮ የተመለሱት ሕዝቡም ሁሉ በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ሥርዐቱን አደረጉ። 7 ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዳሴም ቤት መቶ ኮርማዎችን፥ ሁለት መቶ ፍየሎችና አራት መቶ በጎችን አቀረቡ። 8 ስለ እስራኤልም ኀጢአት ሁሉ ማስተስረያ፦ ባሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ሹሞች ቍጥር ዐሥራ ሁለት ሙክቶችን አቀረቡ። 9 ካህናቱና ሌዋውያኑም በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ እንደ ሥርዐታቸው ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር አገልግሎት በየወገናቸው ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው ቆሙ። በረኞችም በየበሮቻቸው ቆሙ። የፋሲካ በዓል 10 ከምርኮ የተመለሱ የእስራኤል ልጆችም በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ። ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ሁሉም ራሳቸውን በአንድነት አንጽተዋልና። 11 ከምርኮ የተመለሱት ልጆቻቸው ግን ሁሉም ሰውነታቸውን አላነጹም ነበር፤ ሌዋውያን ግን ሁሉም ነጽተው ነበርና፤ 12 ከምርኮ ለተመለሱት ለእስራኤል ልጆች ለወንድሞቻቸው ለካህናትና ለራሳቸውም የፋሲካን በግ ሠዉ። 13 ከምርኮ የተመለሱ የእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ እግዚአብሔርንም ይሹት ዘንድ ከምድር አሕዛብ ርኵሰት የተለዩት ሁሉ ፋሲካውን በሉ። 14 በእግዚአብሔርም ፊት ደስ ብሏቸው ሰባት ቀን የቂጣዉን በዓል አከበሩ። 15 እግዚአብሔር የፋርሱን ንጉሥ ልቡና መልሶላችዋልና፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ሥራም እጃቸውን አጽንቶላቸዋልና። |