Este libro no es inspirado por Dios y no forma parte del canon cristiano ni del Tanaj judío. Se muestra solo con fines históricos y de estudio. Ver explicación completa መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ስም ዝርዝር 1 ከዚህም በኋላ የሚወጡትን ያባቶቻቸውን ቤተ ሰቦች አለቆች በየወገኖቻቸው ለዩ፤ ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን፥ ወንዶች አገልጋዮቻቸውንና ሴቶች አገልጋዮቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም ለዩ። 2 ዳርዮስም በመሰንቆ፥ በበገናና በከበሮ በሰላም ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሷቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ሺህ ፈረሰኞችን ላከ። 3 ወንድሞቻቸውም ሁሉ እየዘፈኑ ከእነርሱ ጋር በአንድነት እንዲሄዱ አደረገ። 4 በየሀገራቸውና በየወገናቸው፥ አለቆቻቸውን ተከትለው የወጡ ሰዎችም ስማቸው ይህ ነው። 5 ካህናት የፊንሐስ ልጆች፥ የአሮን ልጆች፥ የሰራህያ ልጅ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢዮስስ፥ ከይሁዳ ወገን ከፋሬስ ወገን ከዳዊት ወገን የሆነ የሰላትያል ልጅ የዘሩባቤል ልጅ ኢዮአቄም፤ 6 ዘሩባቤልም በፋርስ ንጉሥ በዳርዮስ ፊት በሁለተኛው ዓመተ መንግሥቱ በመጀመሪያው ወር በሚያዝያ የጥበብን ነገር የተናገረ ነው። 7 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከፋርስ ምርኮ የወጡ ከይሁዳ የሆኑ ሰዎች እኒህ ናቸው። 8 እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ሌላዎች የይሁዳ ክፍሎች ተመለሱ። ሁሉንም በየከተሞቻቸው ላካቸው፤ እነዚህም አስቀድመው ከተሾሙላቸው ከመጀመሪያዎቹ ሹሞች፥ ከኢያሱና ከዘሩባቤል፥ ከነህምያ፥ ከዛርያስ፥ ከሬስያስ፥ ከኤኔንዮስ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከቦኤልሰሮስ፥ ከአስፈራሶስ፥ ከሬልዮስ፥ ከኢሮምዮስና ከበዓናስ ጋር የመጡ ናቸው። 9 የሕዝቡም ቍጥር፥ የፋሬስ ልጆች ሁለት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ናቸው፤ የሳፋንም ልጆች ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ናቸው። 10 የሐሬስ ልጆችም ሰባት መቶ አምሳ ስድስት ናቸው። 11 የፈሓት ሞዓብ ልጆችም ከሮብአምና ከኢዮስስ ልጆች ጋራ ሁለት ሺ ስምንት መቶ ዐሥራ ሁለት ናቸው። 12 የኤላም ልጆች አንድ ሽህ ሁለት መቶ አምሳ አራት ናቸው፤ የዛጦንም ልጆች ዘጠኝ መቶ ስድሳ ናቸው፤ የኮሮባ ልጆች ሰባት መቶ አምሳ ናቸው፤ የባኒን ልጆችም ስድስት መቶ አርባ ስምንት ናቸው። 13 የቤባይ ልጆችም ስድስት መቶ ሠላሳ ሦስት ናቸው፤ የዓዝጋድ ልጆችም ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ሁለት ናቸው። 14 የአዶኒቃም ልጆች ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የበጉዋይ ልጆችም ሁለት ሺህ ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የአዲኖስም ልጆች አራት መቶ አምሳ አራት ናቸው። 15 የአዝራቅዮ፥ የቄላንና የአዛጦን ልጆች ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የአዛሩ ልጆችም አራት መቶ ሠላሳ ሁለት ናቸው። 16 የሐናንያም ልጆች መቶ አንድ ናቸው፤ የአሮምና የባሕሴ ልጆች ሦስት መቶ ሃያ ሦስት ናቸው፤ 17 የአርስፋሪስት ልጆች አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት ናቸው። የበጢሩስ ልጆችም ሦስት ሽህ አምስት ናቸው፤ የኤናውም ልጆች መቶ አምሳ ስምንት ናቸው። የቤትሎሞን ልጆችም መቶ ሃያ ሦስት ናቸው። 18 ከኒጤባስም ልጆች አምሳ አምስት፥ ከኤናጦስም ልጆች መቶ አምሳ ስምንት፥ የቤትሳሞስ ልጆች አርባ ሁለት፥ 19 የቀታርቲሐርዮስ ልጆችም ሃያ አምስት፥ የጳሬስና የፎሮግ ልጆች ሰባት መቶ አርባ ሦስት ናቸው፤ 20 አካዲያስና አሚዳውያንም አራት መቶ ሃያ ሁለት ናቸው፥ የቂራማና የጋቢስ ልጆች ስድስት መቶ ሃያ አንድ ናቸው። 21 የመቃሉንም ልጆች መቶ ሃያ ሁለት፥ ከቤጠሊም ልጆች አምሳ ሁለት፥ የኔፋስም መቶ አምሳ ስድስት ናቸው። 22 የቀላምሎምና የሁነስ ልጆች ሰባት መቶ ሃያ አምስት፥ የኤሪካ ልጆች ሦስት መቶ አርባ አምስት፤ 23 የሰናሐሰም ልጆች ሦስት ሺህ ሦስት መቶ አንድ ናቸው። 24 የኢዮስስ ልጆች፥ ካህናቱም ከአናሲብ ልጆች ጋራ ስምንት መቶ ሰባ ሁለት ናቸው። የኤምሩት ልጆችም ሁለት መቶ አምሳ ሁለት ናቸው። 25 የፋሰሩ ልጆችም አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት፥ የካርሚ ልጆች ሽህ ዐሥራ ሰባት ናቸው። 26 ሌዋውያን ግን፦ የኢዮስስ የቆድሔሉ፥ የባኑና የሱዱይ ልጆች ሰባ አራት፤ 27 መዝሙር የሚዘምሩ የካህናት ልጆች፦ የአሳፍ ልጆች መቶ ሃያ ስምንት፥ 28 በረኞች የሰሎም ልጆች፦ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሰባይ ልጆች ሁሉም መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ናቸው። 29 የቤተ መቅደስ አገልጋዮች፦ የኤሳው ልጆች፥ የሓሱፋ ልጆች፥ የጠብይት ልጆች፥ የቀራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፥ የፋዶን ልጆች፥ የሌብና ልጆች፤ የአባጋ ልጆች፥ 30 የዐቁድ ልጆች፥ የሐጡ ልጆች፥ የኪጣብ ልጆች፥ የአቀባ ልጆች፥ የሳባዊ ልጆች፥ የሐና ልጆች፥ የቃጡዓ ልጆች፥ የጌዱር ልጆች፤ 31 የያሳሩ ልጆች፥ የዴሳን ልጆች፥ የነሒሴቦ ልጆች፥ የካሴባ ልጆች፥ የቀዚራ ልጆች፥ የዖዝያ ልጆች፥ የፋኑሕ ልጆች፥ የአዛራ ልጆች፥ የባስቲ ልጆች፥ የአስና ልጆች፥ የማአኒ ልጆች፥ የነፋሲ ልጆች፥ የአቁፋ ልጆች፥ የአኪባ ልጆች፥ የአሱር ልጆች፥ የፋራቂም ልጆች፥ የባስሊም ልጆች፤ 32 የሚዳ ልጆች፥ የኩታ ልጆች፥ የሴርያ ልጆች፥ የባርኩስ ልጆች፥ የሴሬር ልጆች፥ የቶምሔ ልጆች፥ የናሲ ልጆች፥ የአጢፍ ልጆች። 33 የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች፦ የአሳፍያት ልጆች፥ የፋሬዳ ልጆች፥ የሐሊ ልጆች፥ የሎዝን ልጆች፥ የያሴዳሔል ልጆች፥ የሳፋት ልጆች፤ 34 የሐጋያ ልጆች፥ የፈቀሬተሰባይ ልጆች፥ የሳሮትዮ ልጆች፥ የማሲያስ ልጆች፥ የጋስ ልጆች፥ የአዱስ ልጆች፥ የሱባስ ልጆች፥ የአፌራ ልጆች፥ የባሩዲስ ልጆች፥ የሳፋጥ ልጆች፥ የአሎም ልጆች፤ 35 እነዚህ ቤተ መቅደሱን የሚያገለግሉ ሁሉና የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች ሁሉ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ናቸው። 36 ከቴልሜሬትና ከቴሌርሳስ የወጡት ሁሉ፥ አለቆቻቸውም ካራኃታንና ከሀለር ናቸው። 37 ሀገራቸውንና ዘመዳቸውን፥ ከእስራኤልም ወገን መሆናቸውን መናገር አልቻሉም። የጡባን ልጆች፥ የዱዳን ልጆች፥ የነቆዲንም ልጆች ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ናቸው። 38 ከካህናቱ ወገን የሆኑ፥ የክህነትን ሥራ የሚሠሩ፥ ተመዝግበው ያልተገኙ፦ የሐብያ ልጆች፥ የአቅቦስ ልጆች፥ ከቤርዜሊ ልጆች ወገን በስሙ የተጠራች አውግያን ያገባ የይሆድስ ልጆች ናቸው። 39 የዘመዶቹ ትውልድ ቍጥር በተጻፈበት መጽሐፍ ትውልዱን ፈልገው አጡ፤ የክህነት አገልግሎቱንም አስተዉት። 40 ነህምያና ሐቴርሳታም፥ የክህነትና የጽድቅ ልብስ የሚለብስ ሊቀ ካህናት እስኪሾሙ ድረስ ከተቀደሰው ነገር ሁሉ እንዳይሰጡት አዘዙአቸው። 41 ከዐሥራ ሁለት ዓመት በላይ ያሉት እስራኤል ሁሉ ከሴቶች አገልጋዮቻቸውና ከወንዶች አገልጋዮቻቸው በቀር አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ። 42 ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻቸውም ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ነበሩ፤ ሴቶችና ወንዶች መዘምራንም ሁለት መቶ አርባ አምስት ነበሩ። 43 ግመሎቹም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ ፈረሶቹም ሰባት ሺህ ሠላሳ ስድስት፥ በቅሎዎችም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥ አህዮችም አምስት ሺ አምስት መቶ ሃያ አምስት ነበሩ። 44 ከሀገሮቻቸው አለቆችም ዐያሌዎች በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደረሱ ጊዜ እንደሚቻላቸው መጠን ቤተ መቅደሱን በቦታው ያቆሙት ዘንድ ጸለዩ። 45 ለቤተ መቅደሱ የሥራ ጣጣም አንድ ሺህ ወቄት ወርቅ፥ አምስት ሺህ ወቄት ብርና መቶ የካህናት ልብስ ወደ ግምጃ ቤቱ ያገቡ ዘንድ ተሳሉ። 46 ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ከሚኖሩ ሕዝቦችም፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹም፥ እስራኤልም ሁሉ በየቦታቸው ይቀመጡ ነበር። ሥርዐተ አምልኮት እንደገና መጀመሩ 47 የእስራኤልም ልጆች በያገራቸው ተቀምጠው ሳሉ በሰባተኛው ወር መባቻ በምሥራቁ በር ዳርቻ ባለው አደባባይ በአንድነት ተሰበሰቡ። 48 የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ወንድሞቹ ካህናት፥ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹም፥ ተነሡ፤ 49 በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ እንደ ሕጉ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ለእስራኤል ፈጣሪ ለእግዚአብሔር መሠዊያውን አዘጋጁ። 50 ሌሎችም የምድር አሕዛብ ከእነርሱ ጋር ተሰብስበው በቦታቸው በመሥዊያው አጠገብ ተዘጋጁ፤ ተሰልፈው ነበርና፤ ከዚህም በኋላ የምድር አሕዛብን አሸነፏቸው፤ በየጊዜው የሚደረገውንም የነግሁንና የሠርኩን መሥዋዕት ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 51 በሕግ እንደ ተጻፈ የዳስ በዓልን አደረጉ፤ በየዕለቱም እንደ ቀድሞው መሥዋዕቱን ሠዉ። 52 ዳግመኛም የዘወትሩን ቍርባንና የሰንበቱን መሥዋዕት፥ የመባቻዎችንና የተቀደሱትን በዓላት መሥዋዕት አቀረቡ። 53 ለእግዚአብሔርም ስእለት የተሳሉ ሰዎች ሁሉ ከሰባተኛው ወር መባቻ ጀምሮ መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ገና አልተሠራም ነበር። 54 ደንጊያ ለሚያለዝቡና እንጨት ለሚጠርቡ ሰዎችም ወርቅና ብር ሰጧቸው፤ ለምግባቸውም መብሉንና መጠጡን ሰጧቸው። 55 የሲዶናና የጢሮስ ሰዎችንም የዋንዛውን እንጨቶች ከሊባኖስ በኢዮጴ ባሕር በኩል በመርከብ ያገቡላቸው ዘንድ አዘዟቸው፤ ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘንድም የትእዛዝ ደብዳቤ ጻፉላቸው። የቤተ መቅደሱ መሠረት እንደ ተጣለ 56 ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቻቸው ካህናቱና፥ ሌዋውያኑም፥ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትም ሁሉ ቤተ መቅደስን ይሠሩ ዘንድ ጀመሩ። 57 ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ በገቡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መባቻ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን መሠረት አኖሩ። 58 ሌዋውያንንም በቤተ እግዚአብሔር ሥራ ላይ ሾሟቸው፤ ኢያሱና ልጆቹ፥ ወንድሞቹም፥ ወንድሙ አድያምያልም፥ የኢያሱ ልጅ ሄሜዴቦን፥ የኤልያዳን ልጅ የይሁዳ ልጆች፥ ከልጆቹና ከወንድሞቹ ጋር ሌዋውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ የሥራ አለቆች ሆነው በአንድነት ተሾሙ። 59 ካህናቱም ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው፥ መሰንቆውንና መለከቱን ይዘው ቆሙ። የአሳፍ ልጆች ሌዋውያንም እግዚአብሔርን በጸናጽል ያመሰግኑ ነበር። 60 በእሴይ ልጅ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መዝሙርም ያመሰግኑት ነበር። 61 ጮኸውም እያስተዛዘሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ምስጋናው ለዘለዓለም ነውና፥ ቸርነቱም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነውና። 62 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመነሣቱ ሕዝቡ ሁሉ መለከቱን እየነፉ፥ ከፍ ባለ ድምፅም እየጮሁ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 63 ቀድሞ በዚያ በያገራቸው ይኖሩ ከነበሩ ከካህናትና ከሌዋውያንም የዚያን ቤት ሥራውን ቀድሞ ያዩት አለቆችም በታላቅ ድምፅ ፈጽመው እያለቀሱ መጡ። 64 ሕዝቡም እስኪሰማ ድረስ ደስ ብሏቸው ቀንደ መለከት የሚነፉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። 65 በሩቅ እስኪሰማ ድረስ በታላቅ ድምፅ ቀንደ መለከት የሚነፉ ብዙ ሰዎች ነበሩና ከሕዝቡ ልቅሶ የተነሣ የመለከቱን ድምፅ አልሰሙም። 66 የይሁዳና የብንያም ወገኖች ጠላቶችም ያን በሰሙ ጊዜ የቀንደ መለከቱ ድምፅ ምን እንደ ሆነ ያውቁ ዘንድ መጡ። 67 ከምርኮ የተመለሱ እስራኤልም የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደሚሠሩ ባወቁ ጊዜ፥ 68 ወደ ዘሩባቤልና ወደ ኢያሱ ወደ አገሮቻቸውም ሹሞች ሄደው እንዲህ አሏቸው፥ “እኛ ከእናንተ ጋራ እንሥራ፥ 69 የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደዚህ ካመጣን ጀምሮ እንደ እናንተ ለፈጣሪያችሁ እንገዛለንና፥ መሥዋዕቱንም ለእርሱ እንሠዋለንና።” 70 ዘሩባቤልና ኢያሱም፥ የየሀገሮቻቸው ሹሞችም እንዲህ አሉአቸው፥ “የእስራኤልን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ለእኛም፥ ለእናንተም አይገባንም፤ 71 ሐጌ እንደ ተናገረ፥ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም እንዳዘዘን የእስራኤልን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እኛ ለብቻችን እንሠራለን።” 72 የሚመክቱ ያገሩ ሰዎች አሕዛብ ግን በይሁዳ ያሉትን ፈጽመው ተሰብስበው ተዋጓቸው። 73 አወኳቸው፤ ሥራቸውንም አስቆሙ፤ በንጉሡ በቂሮስ ዘመንም ሁሉ እንዳይሠሩ ከለከሏቸው፤ እስከ ዳርዮስ ሁለተኛ ዓመተ መንግሥትም ድረስ ሥራውን አስተዉአቸው። |