ሶፎንያስ 3:20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፣ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ሰብስቤ ወደ ሀገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ንብረታችሁን ሁሉ ዐይናችሁ እያየ በምመልስላችሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ዝነኞችና የተመሰገናችሁ ትሆናላችሁ።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም የሚያስጠራ ቦታን እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምንም እሰጣቸዋለሁ።”
ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ሌሎችን እሰበስብለታለሁ” ይላል።
ዘራቸው በአሕዛብ መካከል፥ ልጆቻቸውም በወገኖች መካከል የታወቁ ይሆናሉ፤ ያያቸው ሁሉ እግዚአብሔር የባረካቸው ዘር እንደ ሆኑ ያውቃል፤
እግዚአብሔር፥ “የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተተወች ያይደለች የተወደደች ቅድስት ከተማ” ትባያለሽ።
“እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።
የሕዝቤን ቅሬታ ከበተንኋቸው ምድር ሁሉ ወደ መሰማሪያቸው ሰብስቤ እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይበዛሉ፤ ይባዛሉም።
እገለጥላችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፤ ከአሕዛብ ሁሉ ዘንድ እናንተንም ከበተንሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ እናንተንም ለምርኮ ወዳፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
እነሆ! የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እነርሱም ይገዙአታል።”
ይህችም ከተማ እኔ የምሠራላቸውን በጎነት ሁሉ በሚሰሙ፥ እኔም ስላመጣሁላቸው በጎነትና ሰላም ሁሉ በሚፈሩና በሚደነግጡ አሕዛብ ሁሉ ፊት ለደስታ፥ ለክብርና ለገናንነት ትሆናለች።”
ምርኮአቸውንም እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ እመልሳለሁ፤ በመካከላቸውም ያሉትን የምርኮኞችሽን ምርኮ እመልሳለሁ።
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባቸዋለሁ፤ በአሕዛብና በሕዝብ ፊትም እቀደስባቸዋለሁ፤ ለባሪያዬ ለያዕቆብም በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ።
የጠፋውንም እፈልጋለሁ፤ የባዘነውንም እመልሳለሁ፤ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፤ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም እጠብቃለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።”
ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ! እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፤ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ።
አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የእስራኤልን ልጆች ከገቡባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ፤ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣቸዋለሁ፤
እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አላስቀርም፤
የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የፈረሱትንም ከተሞች ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ የወይን ጠጃቸውንም ይጠጣሉ፤ ተክልን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።
ያዕቆብ ሆይ፥ ሁልንተናህን ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልንም ቅሬታ ፈጽሞ አከማቻለሁ፥ እንደ ባሶራ በጎችና እንደ መንጋ በማሰማርያቸው ውስጥ በአንድነት አኖራቸዋለሁ፥ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
አንካሳይቱንም ለቅሬታ፥ ወደ ሩቅም የተጣለችውን ለብርቱ ሕዝብ አደርጋታለሁ፥ ከዚያም ወዲያ እስከ ዘላለም ድረስ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።
የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ቅሬታ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፣ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳልና በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ።
በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፣ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፣ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።
የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
ከአሕዛብ ሁሉ በላይ ትሆን ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ታላቅ ስምን፥ ምስጋናና ክብርንም አደረገልህ።”