መዝሙር 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለመዘምራን አለቃ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር። 1 ኀጢአተኛ ራሱን የሚያስትበትን ነገር ይናገራል፥ የእግዚአብሔርም ፍርሀት በዐይኖቹ ፊት የለም። 2 በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኀጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል። 3 የአፉ ቃል ዐመፅና ሽንገላ ነው፤ በጎ ሥራን ይሠራ ዘንድ ማስተዋልን አልወደደም። 4 በመኝታው ዐመፅን ዐሰበ፤ በሁሉ ነገር መልካም ባልሆነች መንገድ ቆሞአል፤ ክፋትንም አይሰለቻትም። 5 አቤቱ፥ ምሕረትህ በሰማይ ነው፥ እውነትህም እስከ ደመናት ትደርሳለች። 6 ጽድቅህም እንደ እግዚአብሔር ተራሮች ናት፤ ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ናት። 7 አቤቱ፥ ሰውንና እንስሳን ታድናለህ። አቤቱ፥ ምሕረትህን እንደ አበዛህ፥ የሰው ልጆች በክንፎችህ ጥላ ይታመናሉ። 8 ከቤትህ ጠል ይረካሉ። ከደስታህም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለህ። 9 የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፤ በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን። 10 ምሕረትህን በሚያውቁህ ላይ፥ ጽድቅህንም በልበ ቅኖች ላይ ዘርጋ። 11 የትዕቢት እግር አይምጣብኝ፥ የኀጢአተኛ እጅም አያውከኝ። 12 ዐመፃን የሚያደርጉ ሁሉ በዚያ ይወድቃሉ፤ ይሰደዳሉ፥ መቆምም አይችሉም። |