ኤርምያስ 31:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይመጣሉ፤ በጽዮንም ተራራ ደስ ይላቸዋል፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፥ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ሀገርም ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይራቡም። አዲሱ መደበኛ ትርጒም መጥተውም በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በእግዚአብሔርም ልግስና፣ በእህሉ፣ በወይን ጭማቂውና በዘይቱ፣ በፍየልና በበግ ጠቦት፣ በወይፈንና በጊደር ደስ ይሰኛሉ፤ ውሃ እንደማይቋረጥባት የአትክልት ስፍራ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህም አያዝኑም። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ ላይ ሆነው እልል ይላሉ፤ ስለ ጌታም በጎነቱ፥ ስለ እህሉና ስለ ወይን ጠጁ፥ ስለ ዘይቱም፥ ስለ በጎቹና ስለ ከብቶቹ በሐሤት ይሞላሉ፤ ነፍሳቸውም ውኃ ጠጥታ እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ስለዚህም ተመልሰው መጥተው በጽዮን ተራራ ላይ በደስታ ይዘምራሉ፤ በምሰጣቸውም የእህል፥ የወይን ጠጅ፥ የወይራ ዘይት፥ የበግና የቀንድ ከብት በረከት ሁሉ ተድላ ደስታ ያደርጋሉ፤ በቂ ውሃ እንዳገኘች የተክል ቦታ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ ወዲያም አያዝኑም። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ እልል ይላሉ፥ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ይሰበሰባሉ፥ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። |
በእግዚአብሔር የተሰበሰቡም ይመለሳሉ፤ በደስታም ተመልሰው ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘለዓለም ደስታም በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታንም ያገኛሉ፤ መከራ፥ ኀዘንና ትካዜም ይጠፋሉ።
እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ።
እነሆ፥ የሚጠብቁሽ ሰዎች ድምፅ ከፍ ከፍ ይላልና፥ እግዚአብሔርም ጽዮንን ይቅር ባላት ጊዜ ዐይን በዐይን ይተያያሉና በአንድነት በቃላቸው ደስ ይላቸዋል።
እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ እንደ ነፍስህም ፍላጎት ያጠግብሃል፤ አጥንትህንም ያለመልማል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ።
እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ያልፋልና፤ ፀሐይሽ ከዚህ በኋላ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም አይቋረጥም።
እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤትን አደርጋለሁ፤ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ በውስጥዋ አይሰማም።
ከዳተኞች ልጆች ሆይ! እኔ እገዛችኋለሁና ተመለሱ፤ ይላል እግዚአብሔር። አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፤ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፤
የእስራኤል ድንግል ሆይ እንደ ገና እሠራሻለሁ፤ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ትወጫለሽ።
በኤፍሬም ተራሮች ላይ የሚከራከሩ፦ ተነሡ፤ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጠሩባት ቀን ትመጣለችና።”
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የያዕቆብ ቤት ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ በአሕዛብም አለቆች ላይ እልል በሉ፤ አውሩ፤ አመስግኑም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ።
የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ሰዎች በዚህ ምድር ቤትንና እርሻን የወይን ቦታንም እንደ ገና ይገዛሉ።”
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ባድማ ሆኖ፥ ያለ ሰውና ያለ እንስሳ ባለው በዚህ ስፍራ በከተሞችም ሁሉ መንጎቻቸውን የሚያሳርፉበት የእረኞች መኖሪያ ይሆናል።
በደጋው ላይ ባሉ ከተሞች፥ በቆላውም ባሉ ከተሞች፥ በደቡብም ባሉ ከተሞች፥ በብንያምም ሀገር፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ ስፍራዎች፥ በይሁዳም ከተሞች በጎቹ በተቈጣጣሪያቸው እጅ እንደ ገና ያልፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።”
ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ እተክለዋለሁ፤ ቅርንጫፎችንም ያወጣል፤ ፍሬም ያፈራል፤ ታላቅም ዝግባ ይሆናል፤ በበታቹም ወፎች ሁሉ ያርፋሉ፤ በቅርንጫፎቹም ጥላ በክንፍ የሚበርር ሁሉ ይጠጋል፤ ቅርንጫፉም ይሰፋል።
“በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው ለዘለዓለም ይገዙልኛል፤ በዚያም እቀበላችኋለሁ፤ በዚያም ቀዳምያታችሁን፥ በኵራታችሁንም፥ የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እጐበኛለሁ።
በመልካም ማሰማርያ አስማራቸዋለሁ፤ ጕረኖአቸውም በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ።
ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን እግዚአብሔርንና ቸርነቱን ያስቡታል።
“በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ተራሮች ማርን ያንጠባጥባሉ፤ ኮረብቶችም ወተትን ያፈስሳሉ፤ በይሁዳም ያሉት ፈፋዎች ሁሉ ውኃን ያጐርፋሉ፤ ከእግዚአብሔርም ቤት ምንጭ ትፈልቃለች፤ የሰኪኖንንም ሸለቆ ታጠጣለች።
ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፣ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፣ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ።
እናንተም ዛሬ ታዝናላችሁ፤ እንደገናም አያችኋለሁ፤ ልባችሁም ደስ ይለዋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።
ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን?
እንባዎችንም ሁሉ ከዐይኖቻቸው ያብሳል፤ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ ሐዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፤ የቀደመው ሥርዐት አልፎአልና፤” ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፤ ወደ ሕይወትም ውሃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል።”