ኢሳይያስ 61:3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድም ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታ ለክብሩ የተከላቸው ጽድቃዊ የባሉጥ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች በአመድ ፋንታ አክሊልን እንዳደርግላቸው፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጐናጸፊያ እንድሰጣቸው ልኮኛል። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም በጽዮን ለሚያለቅሱት ሰዎች በዐመድ ፈንታ የአበባ ጒንጒንን፥ በእንባቸው ምትክ የወይራ ዘይትን በኀዘን ፈንታ የደስታ ዘይትን፥ በዛለ መንፈሳቸው ፈንታ የምስጋና መጐናጸፊያን ለማስገኘት ላከኝ። እነርሱም ክብሩን እንዲገልጡ እግዚአብሔር የተከላቸው “የጽድቅ ዋርካዎች” ተብለው ይጠራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘንም መንፈስ ፋንታ የምሥጋናን መጐናጸፊያ እሰጣቸው ዘንድ ልኮኛል። |
በዚያም ቀን እንዲህ ትላለህ፥ “አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ ዳግመኛም ይቅር ብለኸኛልና አመሰግንሃለሁ።
እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ምሕረትን አድርጎአልና ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና የምድር መሠረቶች መለከትን ይንፉ፤ ተራሮችና ኮረብቶች በውስጣቸው ያሉ ዛፎች ሁሉ፥ እልል ይበሉ።
ጽድቄን አመጣኋት፤ ከእኔ ዘንድ የምትገኝ መድኀኒትንም አላዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኀኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።
ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፤ ጽዮን ሆይ፥ ኀይልሽን ልበሺ፤ አንቺም ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንቺ አያልፍምና ክብርሽን ልበሺ።
በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ ይላቸዋል። ነፍሴም በእግዚአብሔር ሐሤት ታደርጋለች። ሽልማትን እንደ ለበሰ ሙሽራ፥ በጌጥ ሽልማቷም እንዳጌጠች ሙሽራ፥ የማዳንን ልብስ አልብሶኛልና፥ የደስታንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛልና።
በዚያን ጊዜም ደናግሉ በዘፈን ደስ ይላቸዋል፤ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ እኔም ልቅሶአቸውን ወደ ደስታ እመልሳለሁ፤ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ።
የሰላምን ተክል አቆምላቸዋለሁ፤ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም።
ደግሞ፦ ንጹሕ ጥምጥም በራስ ላይ አድርጉ አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም አደረጉ፥ ልብስንም አለበሱት፣ የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር።
አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤’
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝኑማላችሁ፤ ዓለምም ደስ ይለዋል፤ እናንተ ግን ታዝናላችሁ፤ ነገር ግን ኀዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።
በእግዚአብሔር ሥራ እንተባበራለንና፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ።
“ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃንም ጠላህ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ እንዳንተ ካሉት ይልቅ የሚበልጥ የደስታ ዘይትን ቀባህ።”
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤