ቈላስይስ 1:6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ይህም ወደ እናንተ የደረሰውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ከአያችሁበት ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያድግና ያፈራ ዘንድ ነው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ይህም ወደ እናንተ ደርሷል። ይህንም ወንጌል ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርን ጸጋ በእውነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ በዓለም ዙሪያ እየሠራ እንዳለ ሁሉ በእናንተም ዘንድ ፍሬ እያፈራና እያደገ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ይህም ወንጌል ወደ እናንተ ደርሶአል፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ መካከል እንደ ሆነው እንዲሁ በመላው ዓለም ፍሬ ያፈራል፤ ያድጋልም። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ ወንጌልን ከሰማችሁበትና የእግዚአብሔርንም ጸጋ እውነተኛነት ከተረዳችሁበት ቀን ጀምሮ ይህ ወንጌል በእናንተ መካከል እንደሆነው በመላው ዓለም በማፍራትና በማደግ ላይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ይህም በዓለም ሁሉ ደግሞ እንዳለ ወደ እናንተ ደርሶአል፥ የእግዚአብሔርንም ጸጋ በእውነት ከሰማችሁበትና ካወቃችሁበት ቀን ጀምሮ፥ በእናንተ ደግሞ እንዳለ እንዲህ በዓለም ፍሬ ያፈራል ያድግማል። |
እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም፥ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።”
እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም፤ እንድትሄዱ፥ ፍሬም እንድታፈሩ፥ ፍሬአችሁም እንዲኖር፤ አብንም በስሜ የምትለምኑት ነገር ቢኖር ሁሉን እንዲሰጣችሁ ሾምኋችሁ።
ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ በመንፈስና በእውነት ለአብ የሚሰግዱባት ጊዜ ትመጣለች፤ እርስዋም አሁን ናት። አብ እንዲህ የሚሰግዱለትን ይሻልና።
ይህንም በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፥ “እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሓን ሰጣቸው እንጃ” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
በመካከላቸውም ቀይ ሐር የምትሸጥ ከትያጥሮን ሀገር የመጣች እግዚአብሔርን የምትፈራ አንዲት ሴት ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልቡናዋን ከፍቶላት ነበርና ጳውሎስ የሚያስተምረውን ታዳምጥ ነበር፤ ስምዋም ልድያ ይባል ነበር።
ይኸውም ዐይናቸውን ትከፍትላቸው ዘንድ፥ ከጨለማም ወደ ብርሃን፥ ሰይጣንን ከማምለክም ወደ እግዚአብሔር ትመልሳቸው ዘንድ፥ ኀጢአታቸውም ይሰረይላቸው ዘንድ፥ በስሜም በማመን ከቅዱሳን ጋር አንድነትን ያገኙ ዘንድ ነው።’
ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ፥ በሌሎች አሕዛብ እንደ ሆነ በእናንተም ዋጋዬን አገኝ ዘንድ ሁልጊዜ ወደ እናንተ ልመጣ እንደ ወደድሁ፥ እስከ ዛሬ ድረስም እንደ ተሳነኝ ልታውቁ እወድዳለሁ።
በኀይልና በተአምራት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ድንቅ ሥራን በመሥራትም፥ ከኢየሩሳሌም አውራጃዎች ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እንደ አስተማርሁ፥ የክርስቶስንም ወንጌል ፈጽሞ እንደ ሰበክሁ እናገር ዘንድ እደፍራለሁ።
ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን፥ ራሳችንን የምናመሰግን አይደለምና፤ ነገር ግን የክርስቶስን ሕግ በማስተማር ወደ እናንተ ደርሰናል።
ከእርሱም ጋር አብረን እየሠራን፥ የተቀበላችኋትን የእግዚአብሔር ጸጋ ለከንቱ እንዳታደርጓት እንማልዳችኋለን።
ወደ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፥ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ።
እንግዲህ ከሰማችሁት ከሰማይ በታች በመላው ዓለም ከተሰበከው እኔ ጳውሎስም አዋጅ ነጋሪና መልእክተኛ ሆኜ ከተሾምሁለት፥ ከወንጌል ትምህርት ተስፋ የመሠረታችሁ አቅዋም ሳይናወጥ ጨክናችሁ በሃይማኖት ብትጸኑ፥
ወንጌላችን በኀይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።
ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።
እኛ ግን በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፤ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤
እየመከርኋችሁና የምትቆሙባት ጸጋ እውነትኛ የእግዚአብሔር ጸጋ እንድትሆን እየመሰከርሁላችሁ፥ የታመነ ወንድም እንደ ሆነ በቈጠርሁት በስልዋኖስ እጅ በአጭሩ ጽፌላችኋለሁ።