ሐዋርያት ሥራ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጢሞቴዎስ 1 ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራን ከተማም ደረሰ፤ እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ አባቱ ግን አረማዊ ነበረ። 2 በደርቤንና በልስጥራን በኢቆንዮንም ያሉ ወንድሞች ሁሉ ይመሰክሩለት ነበር። 3 ጳውሎስም ከእርሱ ጋር ይዞት ሊሄድ ወደደ፤ በዚያም ሀገር ስለ አሉት አይሁድ ወስዶ ገረዘው፤ አባቱ አረማዊ እንደ ነበረ ሁሉም ያውቁ ነበርና። 4 በየከተማውም ሲሔዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን ሥርዐት አስተማሩአቸው። 5 አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ፤ ዕለት ዕለትም ቍጥራቸው ይበዛ ነበር። 6 ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በእስያ እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለከለከላቸው ወደ ፍርግያና ወደ ገላትያ አውራጃ ሄዱ፤ 7 ሚስያ በደረሱ ጊዜም ወደ ቢታንያ ሊሄዱ ወደዱ፤ የጌታችን ኢየሱስ መንፈስ ግን አልፈቀደላቸውም። 8 ከሚስያም ዐልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። 9 ለጳውሎስም በሌሊት አንድ መቄዶናዊ ሰው ቁሞ፥ “ወደ እኛ ወደ መቄዶንያ ዕለፍና ርዳን” እያለ ሲማልደው በራእይ ተገለጸለት። 10 ራእዩንም ባየ ጊዜ ወዲያውኑ ወደ መቄዶንያ ልንሄድ ወደድን፤ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር የሚጠራን መስሎናልና። 11 ከጢሮአዳም ወጥተን ወደ ሰሞትራቄ ገባን፤ በማግሥቱም ናጶሊ ወደምትባለው ሀገር በመርከብ መጣን። 12 ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ሄድን፤ ይህችውም የመቄዶንያ ዋና ከተማና የሮም ቅኝ ግዛት ነበረች፤ በዚያችም ሀገር ጥቂት ቀን ሰነበትን። ስለ ሐር ነጋዴዪቱ ሴት 13 በሰንበት ቀንም ከከተማዉ በር ወደ ባሕሩ ዳር ወጣን፤ በዚያ የጸሎት ቤት ያለ መስሎን ነበርና፤ በዚያም ተቀምጠን፥ በዚያ ለተሰበሰቡ ሴቶች እናስተምር ጀመርን። 14 በመካከላቸውም ቀይ ሐር የምትሸጥ ከትያጥሮን ሀገር የመጣች እግዚአብሔርን የምትፈራ አንዲት ሴት ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልቡናዋን ከፍቶላት ነበርና ጳውሎስ የሚያስተምረውን ታዳምጥ ነበር፤ ስምዋም ልድያ ይባል ነበር። 15 እርስዋም ከቤተ ሰቦችዋ ጋር ተጠመቀች፤ “ለእግዚአብሔር አማኝ ካደረጋችሁኝስ ወደ ቤቴ ገብታችሁ እደሩ” ብላ ማለደችን፤ የግድም አለችን። ጋኔን ስለሚጥላት ሴት 16 ለጸሎት ስንሄድም የምዋርተኛነት መንፈስ ያደረባት አንዲት ልጅ አገኘችን፤ በጥንቈላም የምታገኘውን ብዙ እጅ መንሻ ለጌቶችዋ ታገባ ነበር። 17 ከዚህም በኋላ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፥ “እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፤ የሕይወትንም መንገድ ያስተምሩአችኋል” እያለች ትጮኽ ነበር። 18 ብዙ ቀንም እንዲሁ ታደርግ ነበር፤ ጳውሎስንም አሳዘነችው፤ መለስ ብሎም፥ “መንፈስ ርኩስ፥ ከእርስዋ እንድትወጣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝዤሃለሁ” አለው፤ ወዲያውኑም ተዋት። 19 ጌቶችዋም የምታገባላቸው የጥቅማቸው ተስፋ እንደ ቀረ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው በገበያ እየጐተቱ ወደ ገዢዎች ወሰዱአቸው። 20 ወደ ገዢዎችም አቅርበው፥ “እነዚህ ሰዎች ከተማችንን ያሸብሩብናል፤ እነርሱም አይሁድ ናቸው። 21 እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆንም ልናደርገው የማይገባንን ሕግ ይናገራሉ” አሉ። 22 ሕዝቡም ተነሡባቸው፤ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፍፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ። 23 በብዙም ደብድበው አሰሩአቸው፤ የወህኒ ቤቱን ዘበኛም አጽንቶ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። 24 እርሱም ትእዛዙን ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ቤት አስገባቸው፤ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። 25 በመንፈቀ ሌሊትም ጳውሎስና ሲላስ ጸለዩ፤ እግዚአብሔርንም በዜማ አመሰገኑት፤ እስረኞቹም ይሰሙአቸው ነበር። 26 ድንገትም ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፤ የወህኒ ቤቱ መሠረትም ተናወጠ፤ በሮችም ሁሉ ያንጊዜ ተከፈቱ፤ የሁሉም እግር ብረቶቻቸው እየወለቁ ወደቁ። 27 የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ በሮች ሁሉ ተከፍተው አየ፤ ሰይፉንም መዝዞ ራሱን ሊገድል ወደደ፤ እስረኞቹ ያመለጡት መስሎት ነበርና። 28 ጳውሎስም፥ “በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ሁላችንም ከዚህ አለን” ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ። 29 መብራት አምጥቶም እየተንቀጠቀጠ ወደ ውስጥ ሄደና ለጳውሎስና ለሲላስ ወድቆ ሰገደ። 30 ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶች፥ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው። 31 እነርሱም፥ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰብህም ሁሉ ትድናላችሁ” አሉት። 32 የእግዚአብሔርንም ቃል ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ ነገሩአቸው። 33 ወዲያውኑም በሌሊት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ እርሱም በዚያው ጊዜ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ። 34 ወደ ቤቱም አግብቶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በጌታችን ስለ አመነም እርሱ ከቤተ ሰቡ ጋር ደስ አለው። 35 በነጋ ጊዜም፥ ገዢዎቹ፥ “እነዚያን ሰዎች ፈትታችሁ ልቀቋቸው” ብለው ብላቴኖቻቸውን ላኩ። 36 የወህኒ ቤቱ ጠባቂም በሰማ ጊዜ ሄዶ ገዢዎቹ “ይፈቱ” ብለው እንደ ላኩ ይህን ነገር ለጳውሎስና ለሲላስ ነገራቸው፤ “አሁንም ውጡና በሰላም ሂዱ” አላቸው። 37 ጳውሎስ ግን፥ “እኛ የሮም ሰዎች ስንሆን፥ ያለ ፍርድ በአደባባይ ገረፉን፤ አሰሩንም፤ አሁንም በስውር ሊያወጡን ይሻሉ፤ አይሆንም፥ ራሳቸው መጥተው ያውጡን” አላቸው። 38 ብላቴኖቻቸውም ሄደው ይህንን ነገር ለገዢዎቹ ነገሩአቸው፤ የሮም ሰዎች መሆናቸውንም ሰምተው ደነገጡ። 39 መጥተውም ከከተማቸው እንዲወጡ ማለዱአቸው። 40 ከወኅኒ ቤቱም ከወጡ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ገብተው ወንድሞችን አገኙ፤ አጽናንተዋቸውም ሔዱ። |