ሐዋርያት ሥራ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰ ተጨማሪ ስደት 1 በዚያም ወራት ሄሮድስ የቤተ ክርስቲያንን ሹሞች ያዛቸው፤ መከራም አጸናባቸው። 2 የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። 3 አይሁድንም ደስ እንዳላቸው አይቶ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው፤ ያንጊዜም የፋሲካ በዓል ነበር። 4 ይዞም ወኅኒ ቤት አስገባው፤ ለሚጠብቁት ለዐሥራ ስድስቱ ወታደሮችም አሳልፎ ሰጠው፤ ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ሊያቀርበው ወድዶ ነበር። 5 ጴጥሮስንም በወኅኒ ቤት ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ ክርስቲያንም ዘወትር ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር። መልአክ ጴጥሮስን ከወኅኒ ቤት እንደ አወጣው 6 ሄሮድስም ማለዳ ያቀርበው ዘንድ በወደደባት በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ ሁለቱን እጆቹን በሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም የወኅኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። 7 የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ በአጠገቡ ቆመ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን ሆነ፤ ጴጥሮስንም ጎኑን ነክቶ ቀሰቀሰውና፥ “ፈጥነህ ተነሥ” አለው፥ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወልቀው ወደቁ። 8 መልአኩም፥ “ወገብህን ታጠቅ፥ ጫማህንም ተጫማ” አለው፤ እንደ አዘዘውም አደረገ፤ “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ” አለው። 9 ተከትሎትም ወጣ፤ ጴጥሮስ ግን ራእይ የሚያይ ይመስለው ነበረ እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም ነበር። 10 መጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደምትወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ ያንጊዜም መዝጊያው ራሱ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም በአንድ ስላች መንገድ ሄዱ፤ መልአኩም ጴጥሮስን ትቶት ሄደ። 11 ያንጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመለሰለትና፥ “እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ በእውነት አሁን ዐወቅሁ” አለ። 12 ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። 13 ጴጥሮስም በሩን አንኳኳ፤ ሮዴ የምትባል ብላቴናም ልትከፍትለት መጣች። 14 የጴጥሮስም ድምፅ መሆኑን ዐውቃ ከደስታ የተነሣ አልከፈተችለትም፤ ነገር ግን ጴጥሮስ በበር ቆሞ ሳለ ሮጣ ነገረቻቸው። 15 እነርሱም “አብደሻልን? አንድ ጊዜ ታገሺ” አሉአት፤ እርስዋ ግን እርሱ እንደ ሆነ ታረጋግጥ ነበር። እነርሱም፥ “ምናልባት መልአኩ ይሆናል” አሉ። 16 ጴጥሮስ ግን በሩን ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ ከፍተውም ባዩት ጊዜ ተደነቁ። 17 እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመለከታቸው፤ ከወኅኒ ቤትም እግዚአብሔር እንደ አወጣው ነገራቸው፤ “ይህንም ለያዕቆብና ለወንድሞች ሁሉ ንገሩ” አላቸው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። 18 በነጋ ጊዜም ወታደሮች፥ “ጴጥሮስ ምን ሆነ?” ብለው ታወኩ። 19 ሄሮድስ ግን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ። የሄሮድስ ሞት 20 ሄሮድስም በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ተቈጥቶ ነበር፤ በአንድነትም ወደ እርሱ መጥተው የንጉሡን ቢትወደድ በላስጦስን እንዲያስታርቃቸው ማለዱት፤ የሀገራቸው ምግብ ከንጉሥ ሄርድስ ነበርና። 21 ከዚህም በኋላ አንድ ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ፥ በአደባባይ ተገኝቶ ይፈርድ ጀመረ። 22 ሕዝቡም፥ “የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የሰው ቃልም አይደለም” እያሉ ጮኹ። 23 ለእግዚአብሔርም ክብር ስለ አልሰጠ ያንጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሠፈው፤ ተልቶም ሞተ። 24 የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ አለ፤ በዛም። 25 በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም አስከትለውት መጡ። |