ዮናስ 4:8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ፀሐይ ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ ላከ፤ የፀሐዩም ሐሩር ራሱን ስላቃጠለው ዮናስ ተዝለፈለፈ፤ ሞትንም በመመኘት “ከመኖር ይልቅ መሞት ይሻለኛል” አለ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ፀሓይ ስትወጣ፣ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አመጣ፤ ፀሓዩም የዮናስን ራስ አቃጠለ፤ እርሱም ተዝለፈለፈ፤ መሞትም ፈልጎ፣ “ከመኖር መሞት ይሻለኛል” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ፀሐይም በወጣ ጊዜ እግዚአብሔር የሚያቃጥል የምሥራቅ ነፋስ አዘጋጀ፥ ዮናስ ራሱን እስኪስት ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለነፍሱም ሞትን ለመነና “ከሕይወት ሞት ይሻላል” አለ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ፀሐይም በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ትኩስ የምሥራቅ ነፋስን አዘዘ፤ ዮናስንም እስኪዝል ድረስ ፀሐይ ራሱን መታው፤ ለራሱም ተስፋ ቈርጦ፥ “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ። |
ኤልያስ አንድ ቀን ሙሉ በበረሓ ተጓዘ፤ ከዚህ በኋላ ጒዞውን ቆም አድርጎ፥ በአንድ የክትክታ ዛፍ ጥላ ሥር ተቀመጠ፤ ሞቱንም በመመኘት “እግዚአብሔር ሆይ! አሁንስ ይብቃኝ፤ ከቀድሞ አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ!” ሲል ጸለየ።
አክዓብ፥ የእዝራኤላዊው ናቡቴ “ከአባቶቼ የወረስኩትን ለአንተ አልሰጥህም!” ስላለው በንዴት እየተበሳጨ ወደ ቤቱ ገባ፤ ፊቱንም ወደ ግድግዳ አዙሮ በአልጋው ላይ ተጋደመ፤ ምግብ መብላትም አልፈቀደም።
ኢዮብም “እንዴት የሞኝ ሴት ንግግር ትናገሪያለሽ? እግዚአብሔር መልካም ነገር ሲሰጠን በደስታ እንቀበላለን፤ ታዲያ፥ መከራ ሲያመጣብን በእርሱ ላይ ማጒረምረም ይገባናልን?” አላት። ኢዮብ ምንም እንኳ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ቢደርስበት በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር በመናገር ኃጢአት አልሠራም።
መልኬን ያጠቈረው የፀሐይ ቃጠሎ ነው፤ ስለዚህ ጥቊር በመሆኔ አትናቁኝ፤ የእናቴ ልጆች የሆኑ ወንድሞቼ ስለ ተጣሉኝ የወይን ተክል ጠባቂ አደረጉኝ፤ ስለዚህ የግሌ የወይን ተክል ለመጠበቅ ጊዜ አልነበረኝም።
መራብና መጠማትም አይደርስባቸውም፤ የሚያቃጥል ነፋስ ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም፤ ይህም የሚሆነው የሚራራላቸው እርሱ የውሃ ምንጭ ወደሚገኝበት ቦታ ስለሚመራቸው ነው።
ነገር ግን በቊጣ ከስሩ ተነቅሎ ወደ ምድር ተጣለ። ከበረሓ የሚነሣ የምሥራቅ ነፋስ አደረቀው፤ ፍሬዎቹም ረገፉ፤ ብርቱ የሆኑት ቅርንጫፎቹም ደረቁ፤ እሳትም በላቸው።
በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆንም የእግዚአብሔር ቅጣት የሆነው የምሥራቁ ነፋስ ከምድረ በዳ ተነሥቶ ይመጣል፤ ምንጩ ይቆማል፤ ወንዙም ይደርቃል። ነፋሱም የነበሩትን ውድ ዕቃዎች ሁሉ ገፎ ይወስድበታል።
ሙሴም አሮንን “እግዚአብሔር ‘በፊቴ ቀርቦ የሚያገለግለኝ ሁሉ ቅድስናዬን ያክብር፤ እኔም በሕዝቤ ፊት የተከበርኩ እሆናለሁ’ እያለ በተናገረበት ጊዜ ይህንኑ ማስጠንቀቁ ነበር” አለው። አሮንም መልስ ሳይሰጥ ዝም አለ።
እግዚአብሔር ግን በባሕሩ ላይ ከባድ ነፋስን አስነሣ፤ በባሕሩም ላይ የተቀሰቀሰው ማዕበል ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች፤
እግዚአብሔርም “ስለዚህች ቅል ልትበሳጭ ይገባሃልን?” አለው። ዮናስም “በእርግጥ መበሳጨት ይገባኛል፤ እንዲያውም በንዴት እስከምሞት ድረስ መበሳጨት አለብኝ!” አለ።
‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’
ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ሁሉንም ነገር ለዔሊ አስረዳው፤ ሰውሮ ያስቀረው ምንም ነገር አልነበረም፤ ዔሊም “እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም መልካም መስሎ የታየውን ነገር ያድርግ” አለ።