መዝሙር 121 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ጠባቂአችን መሆኑ 1 እኔ ወደ ተራራዎች እመለከታለሁ፤ ታዲያ፥ ርዳታ የማገኘው ከወዴት ነው? 2 ርዳታዬ የሚመጣው ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር ነው። 3 ጠባቂህ ዘወትር ንቁ ስለ ሆነ እንድትሰናከል አያደርግህም። 4 የእስራኤል ጠባቂ ከቶ አያንቀላፋም፤ ፈጽሞም አይተኛም። 5 እግዚአብሔር ጠባቂህ ነው፤ በቀኝህም ሆኖ ያጠላልሃል። 6 ፀሐይ በቀን፥ ጨረቃም በሌሊት ጒዳት አያደርሱብህም። 7 እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ሕይወትህንም በሰላም ይጠብቃል። 8 ከቤትህ ወጥተህ ስትሄድና ወደ ቤትህም ስትመለስ ዛሬም ለዘለዓለሙ ይጠብቅሃል። |