Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


መዝሙር 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሰው መከራ ሲደርስበት የሚያቀርበው ኑዛዜ

1 እኔ “ድርጊቴንና አንደበቴን ከኃጢአት እጠብቃለሁ፤ በአጠገቤ ክፉ ሰው በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ አፌን እሸብባለሁ” ብዬ ቃል ገባሁ።

2 አንድ ቃል እንኳ ሳልናገር ዝም አልኩ፤ መልካም ስለ ሆነ ነገር እንኳ አልተናገርኩም፤ ነገር ግን ሥቃዬ ከበፊት ይልቅ እየባሰ ሄደ።

3 ልቤ በውስጤ ነደደ፤ በሐሳቤም እሳት ተያያዘ፤ ከዚያም መናገር ጀመርኩ።

4 “ጌታ ሆይ! መጨረሻዬንና የቀኖቼን ብዛት እንዳውቅ አድርገኝ፤ ዕድሜዬም ምን ያኽል አጭር እንደ ሆነ ንገረኝ።”

5 የዘመኔን መለኪያ ከእጅ መዳፍ እንዳይበልጥ አድርገህ አሳጠርከው፤ ዕድሜዬም በአንተ ፊት ከምንም አይቈጠርም፤ በእርግጥ የሰው ሕይወት እንደ ነፋስ ሽውታ ነው።

6 ሰው ከጥላም የተሻለ አይደለም፤ በከንቱ ይደክማል፤ ሀብትን ያከማቻል፤ ነገር ግን ማን እንደሚጠቀምበት አያውቅም።

7 እግዚአብሔር ሆይ! ታዲያ፥ እኔ ተስፋዬን በአንተ ላይ ከማድረግ በቀር ሌላ ምን እጠብቃለሁ?

8 ከኃጢአቴ ሁሉ አድነኝ፤ ሞኞች እንዲሳለቁብኝ አታድርግ።

9 ይህ ሁሉ እንዲደርስብኝ ያደረግኸው አንተ ስለ ሆንክ ዝም እላለሁ፤ አንድ ቃል እንኳ አልናገርም።

10 ከጽኑ አመታትህ የተነሣ በጣም ስለ ተዳከምኩ መቅሠፍትህን ከእኔ አርቅ።

11 ሰውን በኃጢአቱ ትገሥጸዋለህ፤ ትቀጣዋለህም፤ የሚወደውንም ነገር እንደ ብል ታጠፋበታለህ፤ በእርግጥ ሰው ከነፋስ ሽውታ የሚሻል አይደለም።

12 እግዚአብሔር ሆይ! ጸሎቴን ስማ፤ ጩኸቴንም አድምጥ፤ ሳለቅስም ቶሎ ብለህ እርዳኝ፤ እኔ ለጥቂት ጊዜ የአንተ እንግዳ ነኝ፤ እንደ ቀድሞ አባቶቼም በስደተኛነት የምኖር ነኝ።

13 ወደማልመለስበት ወደ ሞት ሳልሄድ ጥቂት ደስታ እንዳገኝ እባክህ ታገሠኝ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos