Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘሌዋውያን 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ናዳብና አቢሁ የፈጸሙት በደል

1 ናዳብና አቢሁ የተባሉት ሁለቱ የአሮን ልጆች እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ወስደው፥ የእሳት ፍም ጭረው ጨመሩበት፤ በእርሱም ላይ ዕጣን አድርገው ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ፤ ያን ዐይነት እሳት ያቀርቡ ዘንድ እግዚአብሔር ስላላዘዛቸው፤ ያ እሳቱ የተቀደሰ አልነበረም፤

2 ከዚህም የተነሣ በድንገት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ እሳት ስለ በላቸው በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤

3 ሙሴም አሮንን “እግዚአብሔር ‘በፊቴ ቀርቦ የሚያገለግለኝ ሁሉ ቅድስናዬን ያክብር፤ እኔም በሕዝቤ ፊት የተከበርኩ እሆናለሁ’ እያለ በተናገረበት ጊዜ ይህንኑ ማስጠንቀቁ ነበር” አለው። አሮንም መልስ ሳይሰጥ ዝም አለ።

4 ሙሴም ዑዚኤል የተባለው የአሮን አጐት ልጆች የሆኑትን ሚሻኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ “ኑ የእነዚህን የወንድሞቻችሁን ሬሳ ከተቀደሰው ድንኳን አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጪ አውጡ” አላቸው።

5 እነርሱም ልብሰ ተክህኖአቸውን ሳያወልቁ መጥተው ሬሳዎቹን ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት ከሰፈር ወደ ውጪ አወጡ።

6 ከዚህ በኋላ ሙሴ አሮንን፥ እንዲሁም አልዓዛርና ኢታማር የተባሉትን ሁለቱን የአሮንን ልጆች እንዲህ አላቸው፤ “ለሐዘን ብላችሁ ጠጒራችሁን አትላጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ይህን ብታደርጉ ግን ትሞታላችሁ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ቊጣውን ያወርዳል፤ ነገር ግን ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ከእግዚአብሔር በተላከ እሳት ስለሞቱት ልጆች እንዲያለቅሱ ተፈቅዶላቸዋል።

7 እግዚአብሔር ባዘዘው የቅባት ዘይት የተቀደሳችሁ ስለ ሆነ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ውጪ አትውጡ፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ፤” አላቸው፤ እነርሱም ሙሴ እንዳዘዛቸው አደረጉ።


የካህናት መመሪያ ሕግ

8 እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፥

9 “አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥታችሁ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዳትገቡ ተጠንቀቁ፤ ይህን ብታደርጉ ትሞታላችሁ፤ ይህም ሕግ ከእናንተ በኋላ በሚነሣውም ትውልድ ዘንድ ሁሉ ተጠብቆ መኖር አለበት።

10 እናንተ በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በንጹሕና ርኩስ በሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አለባችሁ፤

11 በሙሴ አማካይነት እግዚአብሔር የሰጠውን ድንጋጌ ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ አስተምሩ።”

12 ሙሴም አሮንንና ከሞት የተረፉትን ሁለቱን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታማርን እንዲህ አላቸው፦ “ለእግዚአብሔር ከቀረበው የምግብ መባ የተረፈውን ወስዳችሁ እርሾ ያልነካው ቂጣ ጋግሩ፤ እርሱም እጅግ የተቀደሰ መባ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት።

13 ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የምግብ መባ ተከፍሎ ለአንተና ለልጆችህ የተመደበ ድርሻ ስለ ሆነ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት። ይህን እንድታደርጉ እግዚአብሔር አዞኛል።

14 ነገር ግን በመወዝወዝ ልዩ መባ ሆኖ ለእግዚአብሔር ከቀረበ በኋላ የካህናቱ ድርሻ እንዲሆን ስለ ተፈቀደ ፍርምባውንና ወርቹን አንተና ቤተሰብህ ሴቶች ልጆችህ ጭምር ትበሉታላችሁ፤ ይህንንም በተቀደሰ ስፍራ ትበሉታላችሁ፤ ይህም የእስራኤል ሕዝብ የአንድነት መሥዋዕት አድርገው ከሚያቀርቡት መባ ሁሉ ተከፍሎ ለአንተና ለልጆችህ ተሰጥቶአል።

15 ስቡ ለእግዚአብሔር የምግብ መባ ሆኖ በሚቀርብበት ጊዜ ወርቹንና ፍርምባውን ያመጣሉ፤ ይህም ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘለዓለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።”

16 ሙሴ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት በመሆን ቀርቦ የነበረውን ፍየል ምን እንዳደረጉት በጠየቀ ጊዜ ተቃጥሎ እንደ ነበር ተረዳ፤ ይህም ነገር በአልዓዛርና በኢታማር ላይ ሙሴን ስላስቈጣው እንዲህ ሲል ጠየቀ፥

17 “ስለ ኃጢአት ስርየት የቀረበውን መባ ስለምን በተቀደሰ ስፍራ አልበላችሁትም፤ እርሱ እጅግ የተቀደሰ ነው፤ እርሱንም የሕዝቡ ኃጢአት ማስወገጃ እንዲሆን እግዚአብሔር ለእናንተ ሰጥቶአችኋል፤

18 ደሙ ወደተቀደሰው ድንኳን ስላልገባ እኔ ባዘዝኳችሁ መሠረት በዚያው በተቀደሰው ስፍራ የቀረበውን መሥዋዕት መመገብ ነበረባችሁ።”

19 አሮንም “ስለ ኃጢአት ስርየት የቀረበውን መሥዋዕት ዛሬ በልቼው ቢሆን ኖሮ ለካ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኝ ኖሮአልን? እነሆ ሕዝቡ ዛሬ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርበውን መሥዋዕትና የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አምጥተዋል፤ ነገር ግን እነዚህ እንደዚህ ያሉ ነገሮች በእኔ ላይ ደረሱ” ሲል መለሰ፤

20 ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ በተሰጠው መልስ ተደሰተ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos