Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዮናስ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዮናስ አለመታዘዝ

1 እግዚአብሔር ለአሚታይ ልጅ ለዮናስ የገለጠለት የትንቢት ቃል ይህ ነው፦

2 “ተነሥተህ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ እኔ የሕዝብዋን ክፋት ተመልክቼአለሁ። ድምፅህንም ከፍ አድርገህ እርስዋን በመገሠጽ ተናገር።”

3 ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ለመኰብለል አስቦ ወደ ተርሴስ ለመሄድ ተነሣ፤ ወደ ኢዮጴም ወርዶ ከዚያ ወደ ተርሴስ የምትጓዝ መርከብ አገኘ፤ ለጒዞ የሚያስፈልገውንም ዋጋ ከከፈለ በኋላ ወደ መርከቢቱ ገባ፤ ሐሳቡም ከእግዚአብሔር ለመሸሽ ነበር።

4 እግዚአብሔር ግን በባሕሩ ላይ ከባድ ነፋስን አስነሣ፤ በባሕሩም ላይ የተቀሰቀሰው ማዕበል ብርቱ ከመሆኑ የተነሣ መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች፤

5 መርከበኞቹም እጅግ ስለ ፈሩ እያንዳንዱ ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱን ክብደት ለመቀነስ አስበው በውስጥዋ የነበረውን ዕቃ እያወጡ ወደ ባሕር ጣሉ፤ ዮናስ ግን በመርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ በመተኛቱ በከባድ እንቅልፍ ላይ ነበር።

6 የመርከብ አዛዡም ወደ እርሱ ቀርቦ “እንዴት ትተኛለህ? ኧረ እባክህ ተነሥና ወደ አምላክህ ጸልይ፤ ምናልባት ራርቶልን ሕይወታችንን ያድን ይሆናል” አለው።

7 በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩትም ሁሉ እርስ በርሳቸው “በዚህ አደጋ ላይ እንድንወድቅ ምክንያት የሆነው ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ኑ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወጣ።

8 ስለዚህ ዮናስን “እስቲ ንገረን! ይህ ሁሉ አደጋ የመጣብን በማን ምክንያት ይመስልሃል? ለመሆኑ ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴት መጣህ? አገርህስ የት ነው? የየትኛው ሕዝብ ወገን ነህ?” አሉት።

9 ዮናስም “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ የብስንና ባሕርን የፈጠረውን የሰማይ አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” ሲል መለሰላቸው።

10 አስቀድሞ በነገራቸው መሠረት ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት የኰበለለ መሆኑን ዐወቁ፤ ስለዚህም በጣም ፈርተው “ይህን ያደረግኸው ለምንድን ነው?” አሉት።

11 የባሕሩም ማዕበል እየበረታ በመሄዱ መርከበኞቹ “ይህ ማዕበል ጸጥ እንዲል በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲሉ ጠየቁት።

12 ዮናስም “ይህ ማዕበል በእናንተ ላይ የመጣው በእኔ በደል ምክንያት እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ እኔን አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፤ ማዕበሉም ጸጥ ይልላችኋል” አላቸው።

13 መርከበኞቹ ግን ባላቸው ኀይል ሁሉ እየቀዘፉ መርከቢቱን ወደ ዳር ለማድረስ ሞከሩ፤ ሆኖም ማዕበሉ እጅግ በርትቶ ስለ ነበር ይህን ማድረግ አልቻሉም።

14 ስለዚህ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! የዚህ ሰው ሕይወት እንዲጠፋ ብናደርግ አታጥፋን፤ አንተ የፈቀድከውን ስላደረግህ ንጹሕ ደም እንዳፈሰስን አድርገህ አትቊጠርብን!” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

15 ከዚህ በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት፤ የባሕሩም ማዕበል ጸጥ አለ።

16 በዚህም ሁኔታ መርከበኞቹ እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈሩ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስእለትንም ተሳሉ።

17 አንድ ትልቅ ዓሣ ዮናስን እንዲውጥ ከእግዚአብሔር ታዘዘ፤ ስለዚህም ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ኖረ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos