ዘፍጥረት 42:21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ተገቢውን ቅጣት በመቀበል ላይ ነን፤ ምሕረት እንድናደርግለት ተጨንቆ ሲለምነን ልመናውን አልተቀበልንም ነበር፤ በእኛም ላይ ይህ ጭንቀት ሊደርስብን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርስ በርሳቸውም፣ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማፀነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እርስ በርሳቸውም፥ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፥ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፥ “በእውነት ወንድማችንን በድለናል፤ እኛን በመማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እንዲህም አደረጉ። እነርሱ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፦ በእውነት ወንድማችንን በድለናል እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን። |
ይሁዳም “እንግዲህ ለጌታችን ምን መልስ እንሰጣለን? ራሳችንን ነጻ የምናደርግበት መልስ መስጠት ከቶ አንችልም፤ እግዚአብሔር የሠራነውን በደል ገልጦታል፤ እንግዲህ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሪያዎችህ እንሁን” አለ።
ዮሴፍ ወንድሞቹን “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወት አለን?” አላቸው። ወንድሞቹ የተናገረውን በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ መልስ መስጠትም ተሳናቸው።
የዮሴፍ ወንድሞች አባታቸው ከሞተ በኋላ “ዮሴፍ ባደረስንበት በደል ሁሉ እስከ አሁንም ቂም ይዞ ሊበቀለን ቢፈልግ ምን እናደርጋለን?” ተባባሉ።
እርስዋም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ስለምን ይህን አደረግህብኝ? ወደዚህ የመጣኸው ኃጢአቴን አስታውሰህ ልጄ እንዲሞትብኝ ለማድረግ ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
እነሆ የራስሽ ክፋት ይቀጣሻል፤ ክሕደትሽ ይፈርድብሻል፤ እኔን አምላክሽን እግዚአብሔርን መተውሽና ለእኔም የምታሳዪውን ክብር ማስቀረትሽ ምን ያኽል ከባድና መራራ በደል እንደ ሆነ ትረጂአለሽ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ ነኝ።”
እነሆ እኔ እግዚአብሔር እናንተንም የምላችሁ ይህ ነው፦ ‘አልታዘዛችሁም፤ ወገኖቻችሁ ለሆኑ እስራኤላውያንም ነጻነት አልሰጣችሁም፤’ ስለዚህም እኔ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ ትሞቱ ዘንድ እተዋችኋለሁ፤ በእናንተ ላይ በማደርገውም ነገር የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲሠቀቅ አደርጋለሁ።
ይሁዳ ሆይ! ይህ ሁሉ የደረሰብሽ በአካሄድሽና በክፉ ሥራሽ ምክንያት ነው፤ ይህም ሁሉ የመረረ መከራ የመጣብሽ በኃጢአትሽ ምክንያት ስለ ሆነ ወደ ሰውነትሽ ዘልቆ ልብሽን አቊስሎታል።
ቃላችሁን ባትጠብቁ ግን እግዚአብሔርን የምታሳዝኑ ሆናችሁ እንዳትገኙ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ሰለ ኃጢአታችሁም ቅጣት የሚደርስባችሁ መሆኑንም አትዘንጉ።
አዶኒቤዜቅም “የእጆቻቸውና የእግሮቻቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር ፍርፋሪ እየለቀሙ ይበሉ ነበር፤ በእነርሱ ላይ የፈጸምኩትን ግፍ ዛሬ እግዚአብሔር በእኔ ላይ መልሶ አመጣብኝ” ሲል ተናገረ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተወስዶ በዚያው ሞተ።