ምሳሌ 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 የንጉሥ ልብ በእግዚአብሔር እጅ ነው፤ እርሱንም እንደ ወራጅ ውሃ ወደ ፈቀደው ይመራዋል። የንጉሥንም አእምሮ ይቈጣጠራል። 2 ሰው የሚያደርገው ነገር ሁሉ ትክክል ይመስለዋል፤ እግዚአብሔር ግን የልብን ሐሳብ ይመዝናል። 3 መሥዋዕት ከማቅረብ እውነተኛ ይልቅ ትክክልና የሆነውን ነገር ማድረግ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል። 4 ትዕቢትና ዕብሪት የክፉ ሰዎች መታወቂያ ናቸው፤ ይህም ኃጢአት ነው። 5 በጥንቃቄ በወጣ ዕቅድ የሚሠራ ሥራ ትርፍ ያስገኛል፤ ያለ ዕቅድ በችኰላ የሚሠራ ሥራ ግን ያደኸያል። 6 በመዋሸት የሚገኝ ሀብት ተኖ እንደሚጠፋ እንፋሎትና እንደሚገድል ወጥመድ ነው። 7 ዐመፀኞች መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ስለማይወዱ በግፍ ሥራቸው ይጠፋሉ። 8 ኃጢአተኞች በጠማማ መንገድ መሄድ ይወዳሉ፤ ልበ ንጹሖች ግን መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋሉ። 9 ከጨቅጫቃ ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖር ይልቅ በጣራ ማእዘን ላይ መኖር ይሻላል። 10 ዐመፀኞች ዘወትር ክፋትን ማድረግ ይወዳሉ፤ ለማንም ሰው ርኅራኄ የላቸውም። 11 ፌዘኛ በሚቀጣበት ጊዜ አላዋቂ ሰው ጥበብን ያገኛል፤ ለብልኅም ሰው ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ የበለጠ ዐዋቂ ይሆናል። 12 ጻድቁ አምላክ በክፉዎች ቤት የሚደረገውን ሁሉ ይመለከታል። ክፉዎችንም አሸቀንጥሮ በመጣል ያጠፋቸዋል። 13 የድኾችን ጩኸት ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው እርሱም ተቸግሮ በሚጮኽበት ጊዜ የሚረዳው አያገኝም። 14 የተቈጣ ሰው ስጦታ በድብቅ ሲቀርብለት ንዴቱ ይበርድለታል፤ በምሥጢር የሚሰጥ እጅ መንሻ ቊጣን ያበርዳል። 15 ትክክለኛ ፍርድ በሚሰጥበት ጊዜ ደጋግ ሰዎች ደስ ይላቸዋል፤ ክፉዎችን ግን ያስደነግጣል። 16 ከማስተዋል መንገድ የሚርቀውን ሰው ሞት ይጠብቀዋል። 17 ቅንጦትን የሚወድ ሰው ይደኸያል፤ የወይን ጠጅንና ቅባትን የሚወድድ ሰው ምንጊዜም አይበለጽግም። 18 በደጋግ ሰዎች ላይ ሊደርስ የነበረው ችግር በክፉ ሰዎች ላይ ይደርሳል፤ በቀጥተኛ ሰዎች ላይ ሊደርስ የነበረው ችግር በእምነተ ቢሶች ላይ ይመጣል። 19 ከጨቅጫቃና ከነዝናዛ ሚስት ጋር አብሮ ከመኖር በምድረ በዳ መኖር ይሻላል። 20 ብልኅ ሰው ብዙ ሀብትና ውድ ነገሮችን በቤቱ ያከማቻል፤ ማስተዋል የጐደለው ሰው ግን ያለውን ሁሉ ያባክናል። 21 ጽድቅንና ቸርነትን የሚከተል ሰው ሕይወትን፥ ብልጽግናንና ክብርን ያገኛል። 22 ብልኅ የጦር መሪ በብርቱ ሠራዊት የተጠበቀውን ከተማ ድል አድርጎ ይይዛል፤ የተማመኑባቸውንም ምሽጎች ያፈራርሳል። 23 ከመከራ ለማምለጥ የሚፈልግ፥ ክፉ ከመናገር ይቈጠባል። 24 ትዕቢተኛና ትምክሕተኛ ሰው ፌዘኛ ነው፤ ድርጊቱም በትዕቢት የተሞላ ነው። 25 መሥራት የማይፈልግ ሰነፍ ሰው ራሱን የገደለ ያኽል ይቈጠራል። 26 ሰነፍ ሰው ዘወትር የሚመኘው ብዙ ነገር ለማግኘት ነው፤ ደግ ሰው ግን በልግሥና ይሰጣል። 27 ዐመፀኞች የሚያቀርቡት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፤ በተለይም በክፉ አሳብ ተነሣሥተው የሚያቀርቡለት መሥዋዕት የበለጠ አጸያፊ ነው። 28 የሐሰተኛ ሰው ምስክርነት ውድቅ ይሆናል፤ በጥንቃቄ አስቦ የሚናገር ሰው ቃል ግን ይጸናል። 29 ክፉ ሰው “አልተሳሳትኩም” በማለት በግትርነት ይጸናል፤ እውነተኛ ሰው ግን ስለ ራሱ ጠባይ በጥንቃቄ ያስባል። 30 ሰው በጥበቡ፥ በአስተዋይነቱና በዕቅዱ በእግዚአብሔር ላይ መነሣት አይችልም። 31 ፈረስን ለጦርነት ማዘጋጀት ይቻላል፤ ድልን የሚያጐናጽፍ ግን እግዚአብሔር ነው። |