Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 42 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብጽ መሄዳቸው

1 ያዕቆብ በግብጽ እህል መኖሩን በሰማ ጊዜ ልጆቹን “እርስ በርሳችሁ እየተያያችሁ የምትቀመጡት ለምንድን ነው?

2 በግብጽ አገር እህል መኖሩን ሰምቼአለሁ፤ በራብ እንዳንሞት ወደዚያ ሂዱና እህል ሸምቱልን” አላቸው።

3 ስለዚህ ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ፤

4 ነገር ግን “ጒዳት ይደርስበታል” ብሎ ስለ ፈራ ያዕቆብ ከዮሴፍ ጋር ከአንድ እናት የወለደውን ልጁን ብንያምን ከወንድሞቹ ጋር ወደ ግብጽ አላከውም፤

5 በከነዓን ምድርም ራብ ገብቶ ስለ ነበር የያዕቆብ ልጆች ከሌሎች ሰዎች ጋር እህል ለመሸመት ወደ ግብጽ ሄዱ።

6 ዮሴፍ የግብጽ ምድር አስተዳዳሪ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ ሰዎች ሁሉ እህል እንዲሸጥላቸው ያደርግ ነበር፤ ስለዚህ የዮሴፍ ወንድሞች ወደ እርሱ መጡና ግንባራቸው መሬት እስኪነካ ዝቅ ብለው እጅ ነሡት።

7 ዮሴፍ ወንድሞቹን ባያቸው ጊዜ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን የማያውቃቸው በመምሰል በቊጣ ቃል “ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም “እህል ለመሸመት ከከነዓን አገር መጣን” አሉት።

8 ዮሴፍ ወንድሞቹን ያወቃቸው ቢሆንም እንኳ እነርሱ አላወቁትም ነበር፤

9 ስለ እነርሱ ያየው ሕልም ሁሉ ትዝ አለውና “እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁትም የአገራችንን ደካማነት እምን ላይ እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው።

10 እነርሱም “ጌታችን ሆይ፥ እኛ ሰላዮች አይደለንም፤ እኛ አገልጋዮችህ እዚህ የመጣነው እህል ለመግዛት ነው” አሉት።

11 “እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ የምንታመን ነን፤ ሰላዮችም አይደለንም” አሉት።

12 ዮሴፍም “አይደለም! እናንተ የመጣችሁት የአገራችንን ደካማነት በምን በኩል እንደ ሆነ ለመሰለል ነው” አላቸው።

13 እነርሱም “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን ምድር የሚኖር የአንድ ሰው ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ ወንድማችን ሞቶአል፤ የመጨረሻ ታናሽ ወንድማችን አሁን ከአባታችን ጋር ይገኛል” አሉት።

14 ዮሴፍም እንዲህ አላቸው “ይኸው እኔ እንዳልኩት ያለ ጥርጥር ሰላዮች ናችሁ፤

15 እንግዲህ ታማኝነታችሁ ተፈትኖ የሚረጋገጠው በዚህ ነው፤ ታናሽ ወንድማችሁ እስከሚመጣ ድረስ እንደማልለቃችሁ በንጉሡ በፈርዖን ስም እምላለሁ።

16 ከእናንተ አንዱ ሄዶ ወንድማችሁን ያምጣ፤ የተናገራችሁት እውነት መሆኑ ተረጋግጦ ነጻ እስክትለቀቁ ድረስ የቀራችሁት እዚሁ በእስር ቤት ትቈያላችሁ አለበለዚያ ግን በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ እናንተ ሰላዮች ናችሁ።”

17 ከዚህ በኋላ ሦስት ቀን አስሮ አቈያቸው።

18 በሦስተኛው ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን የምፈራ ሰው ስለ ሆንኩ እንዲህ ብታደርጉ ሕይወታችሁን ታድናላችሁ፤

19 እናንተ ታማኞች ሰዎች ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ እዚሁ በእስር ቤት ይቈይ፤ የቀራችሁት እህሉን ይዛችሁ ወደ ተራቡት ዘመዶቻችሁ ሂዱ።

20 ከዚህ በኋላ ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁልኝ ኑ፤ በዚህ ዐይነት የተናገራችሁት ሁሉ እውነት መሆኑ ይረጋገጣል፤ ከመሞትም ትድናላችሁ።” እነርሱም በዚህ ነገር ተስማሙ፤

21 እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ “በእርግጥ በወንድማችን ላይ ስላደረስነው በደል ተገቢውን ቅጣት በመቀበል ላይ ነን፤ ምሕረት እንድናደርግለት ተጨንቆ ሲለምነን ልመናውን አልተቀበልንም ነበር፤ በእኛም ላይ ይህ ጭንቀት ሊደርስብን የቻለው በዚህ ምክንያት ነው።”

22 ሮቤልም “እኔ በልጁ ላይ ጒዳት እንዳታደርሱ ነግሬአችሁ ነበር፤ ነገር ግን አልሰማችሁኝም፤ እነሆ፥ እርሱን በመግደላችን በቀሉን እየተቀበልን ነው” አላቸው።

23 ዮሴፍ እነርሱ የሚሉትን ሁሉ ያዳምጥ ነበር፤ እነርሱ ግን ከዮሴፍ ጋር የሚነጋገሩት በአስተርጓሚ ስለ ነበር የእነርሱን ንግግር ዮሴፍ እንደሚሰማቸው አላወቁም።

24 ዮሴፍ ከእነርሱ ነጠል ብሎ አለቀሰ፤ እንደገናም ወደ እነርሱ ተመልሶ አነጋገራቸውና ስምዖንን ከመካከላቸው ወስዶ በፊታቸው አሰረው።


የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ከነዓን መመለሳቸው

25 ዮሴፍ አገልጋዮቹን “ለእነዚህ ሰዎች በየስልቻዎቻቸው እህል ሙሉላቸው፤ ገንዘባቸውንም መልሳችሁ በየስልቻዎቻቸው ውስጥ ቋጥሩላቸው፤ ለጒዞአቸውም ስንቅ አስይዙአቸው” ብሎ አዘዘ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፥

26 የዮሴፍ ወንድሞች የገዙትን እህል በአህዮቻቸው ጭነው ጒዞ ጀመሩ።

27 በመንገድ ላይ ሳሉ ለዐዳር በሰፈሩበት ቦታ ከእነርሱ አንዱ ለአህያው ጥሬ ለመስጠት ስልቻውን በፈታ ጊዜ በስልቻው አፍ ላይ ገንዘቡ ተቋጥሮ አገኘው።

28 እርሱም ለወንድሞቹ “ገንዘቤ ተመልሶልኛል፤ ይኸው በስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት!” ብሎ ነገራቸው። ሁሉም በፍርሃት ተንቀጥቅጠው “እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።

29 በከነዓን ወዳለው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ ተመለሱ፤ የደረሰባቸውን ሁሉ እንዲህ ብለው ነገሩት፥

30 “የግብጽ አገር አስተዳዳሪ ‘አገሬን ልትሰልሉ የመጣችሁ ናችሁ’ በማለት በቊጣ ቃል ተናገረን፤

31 እኛም ‘ታማኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤

32 እኛ የአንድ ሰው ልጆች የሆንን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፤ የመጨረሻ ታናሽ ወንድማችን በከነዓን ከአባታችን ጋር አለ’ አልነው።

33 ሰውየውም እንዲህ አለን፤ ‘ታማኞች ሰዎች መሆናችሁን የማውቀው ይህን አንድ ነገር ብታደርጉ ነው፤ ይኸውም ከእናንተ አንዱ ከእኔ ጋር ይቈይ፤ ሌሎቻችሁ ለተራቡት ቤተሰቦቻችሁ እህል ይዛችሁ ወደ አገራችሁ ተመለሱ፤

34 ታናሽ ወንድማችሁንም ይዛችሁልኝ ኑ፤ በዚህ ዐይነት ታማኞች ሰዎች መሆናችሁንና ሰላዮችም አለመሆናችሁን አረጋግጣለሁ፤ ወንድማችሁንም መልሼ እሰጣችኋለሁ፤ በዚህም አገር ቈይታችሁ እንደ ፈለጋችሁ መነገድ ትችላላችሁ።’ ”

35 ከዚህ በኋላ እህላቸውን ከስልቾቻቸው ባራገፉ ጊዜ በየስልቻዎቻቸው ውስጥ ገንዘባቸውን እንደ ተቋጠረ አገኙ፤ እነርሱና አባታቸው የተመለሰውን ገንዘብ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈሩ።

36 በዚህ ጊዜ አባታቸው “ልጆቼን ሁሉ እንዳጣ ትፈልጋላችሁን? ዮሴፍ የለም፤ ስምዖንም የለም፤ አሁን ደግሞ ብንያምን ለመውሰድ ትፈልጋላችሁ፤ በዚህ ሁሉ መከራ የምሠቃየው እኔ ነኝ!” አለ።

37 ሮቤል አባቱን እንዲህ አለው፤ “ብንያምን ወደ አንተ መልሼ ባላመጣው ሁለቱን ወንዶች ልጆቼን ወስደህ ግደላቸው፤ ስለዚህ በእኔ ኀላፊነት ላከው፤ እኔም መልሼ አመጣዋለሁ።”

38 ያዕቆብም “ምንም ቢሆን ከእናንተ ጋር አይሄድም፤ ወንድሙ ሞቶአል፤ የቀረው እርሱ ብቻ ነው፤ በመንገድ አንድ ጒዳት ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እንድወርድ ታደርጉኛላችሁ” አላቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos