Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሆሴዕ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ጣዖት አምልኮ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

1 “ካህናት ሆይ! ይህን ስሙ! እናንተም የእስራኤል ሕዝብ አስተውሉ! እናንተም ንጉሣውያን ቤተሰብ ይህን አድምጡ! እነሆ ፍርድ በእናንተ ላይ መጥቶአል፤ በምጽጳ እንደ ወጥመድ፥ በታቦርም እንደ ተዘረጋ መረብ ሆናችኋል።

2 ዐመፀኞች የግድያ ሥራቸውን አስፋፍተዋል፤ ስለዚህ ሁሉንም እቀጣቸዋለሁ።

3 “እኔ የአንቺን የእስራኤልን ሁኔታ ዐውቃለሁ፤ ከእኔ መሰወር አይቻልሽም፤ በጣዖት አምልኮ ዝሙት ረክሰሻል።”

4 የዝሙት መንፈስ በእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ስላለና እግዚአብሔርንም ስለማያውቁ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ሥራቸው አይፈቅድላቸውም።

5 የእስራኤል ሕዝብ ትምክሕት በራሳቸው ላይ ይመሰክርባቸዋል፤ ኃጢአታቸውም መሰናክል ሆኖ ይጥላቸዋል፤ የይሁዳም ሕዝብ ከእነርሱ ጋር ተሰናክለው ይወድቃሉ።

6 መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ በጎቻቸውንና ከብቶቻቸውን ነድተው እግዚአብሔርን ለመፈለግ ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ስለ ተለያቸው አያገኙትም።

7 እነርሱ ራሳቸው ጣዖት አምላኪዎች ስለ ሆኑ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልተገኙም። ልጆቻቸውም እንደ ጣዖት ልጆች ተቆጥረዋል፤ ስለዚህ በዚህ ወር መባቻ እነርሱም ምድራቸውም አብረው ይጠፋሉ።


በይሁዳና በእስራኤል መካከል ስለሚደረገው ጦርነት

8 ለጦርነት እንዲወጡ በገባዖን የመለከት፥ በራማም የጥሩንባ ድምፅ አሰሙ! በቤትአዌን “የብንያም ነገድ ሆይ! ከአንተ ጋር ነን” እያላችሁ ጩኹ!

9 በቅጣት ቀን እስራኤል ባድማ ትሆናለች፤ ይህም በእርግጥ እኔ በእስራኤል ነገዶች ላይ እንዲደርስ የወሰንኩት ጥፋት ነው።

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የይሁዳ መሪዎች የእስራኤልን ድንበር እንደሚያፈርሱ ሰዎች ሆነዋል፤ ስለዚህ እኔ ቊጣዬን እንደ ጐርፍ ውሃ አወርድባቸዋለሁ።

11 እስራኤል ከንቱ ነገርን በመከተል ላይ ስለ ጸና ጭቈናና ፍትሕ ማጣት ደረሰበት።

12 ስለዚህ ብልና ነቀዝ እህልንና እንጨትን እንደሚያጠፉ እኔም እስራኤልንና ይሁዳን አጠፋለሁ።

13 “እስራኤል መታመሙን፥ ይሁዳም መቊሰሉን ባየ ጊዜ፥ እስራኤል ወደ አሦር ፊቱን መለሰ፤ ርዳታም ለማግኘት ወደ ታላቁ ንጉሥ መልእክተኛ ላከ፤ ነገር ግን እርሱ ሊያድናቸው ወይም ቊስላቸውን ሊፈውስ አልቻለም።

14 ከዚህ የተነሣ እስራኤልን እንደ አንበሳ፥ ይሁዳንም እንደ ደቦል አንበሳ በመሆን ሰባብሬአቸው እሄዳለሁ፤ ነጥቄ እወስዳቸዋለሁ፤ ማንም ሊያድናቸው አይችልም።

15 “መከራ ሲበዛባቸው እኔን ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ የሠሩትን በደል ተገንዝበው ወደ እኔ እስከሚመለሱ፥ ድረስ ከእነርሱ እርቃለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos