Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 44 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ጠፋ የተባለው ዋንጫ በብንያም ስልቻ ውስጥ መገኘቱ

1 ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ “ለመጫን የሚችሉትን ያኽል በየስልቻዎቻቸው ሙላላቸው፤ የእያንዳንዱንም ገንዘብ በየስልቻው አፍ አስቀምጠው።

2 የእኔን የብር ዋንጫ ውሰድና በታናሽ ወንድማቸው ስልቻ ውስጥ እህል ለመሸመት ከመጣው ገንዘብ ጋር ክተተው።” የቤቱም አዛዥ ዮሴፍ እንደ ነገረው አደረገ።

3 ጠዋት በማለዳ ወንድማማቾቹ አህዮቻቸውን ይዘው እንዲሄዱ ተደረገ።

4 ከከተማው ወጥተው ገና ጥቂት መንገድ ርቀው እንደ ሄዱ፥ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ተከታትለህ ያዛቸው፤ ወደ እነርሱም ስትደርስ ‘በመልካም ፈንታ ክፉ የመለሳችሁት ስለምንድን ነው?

5 የጌታዬን የብር ዋንጫ የሰረቃችሁት ለምንድን ነው? ዋንጫው ጌታዬ የሚጠጣበትና ሁሉን ነገር መርምሮ የሚያውቅበት እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህ ያደረሳችሁት በደል እጅግ ከባድ ነው’ ብለህ ንገራቸው።”

6 የቤቱም አዛዥ ወደ ሰዎቹ እንደ ደረሰ ልክ እንደ ተባለው ነገራቸው፤

7 እነርሱም እንዲህ በማለት መልስ ሰጡት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዴት እንዲህ ትናገራለህ? እኛ ይህን የመሰለ ነገር እንዳላደረግን በመሐላ እናረጋግጣለን፤

8 ከአሁን ቀደም በየስልቻችን ያገኘነውን ገንዘብ እንኳ ከከነዓን መልሰን እንዳመጣንልህ ታውቃለህ፤ ታዲያ አሁን ከጌታህ ቤት ብርም ሆነ ወርቅ የምንሰርቀው ለምንድን ነው?

9 ከእኛ አንዱ ይህን ዕቃ ይዞ ቢገኝ በሞት ይቀጣ፤ የቀረነውም የአንተ ባሪያዎች እንሁን።”

10 እርሱም “መልካም ነው፤ እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ፤ ሆኖም ዋንጫውን የወሰደው ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን በነጻ ልትሄዱ ትችላላችሁ” አላቸው።

11 ስለዚህ በፍጥነት ስልቻዎቻቸውን አወረዱ፤ እያንዳንዱም የራሱን ስልቻ ከፈተ።

12 የዮሴፍ አገልጋይ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ የሁሉንም ስልቻ በተራ በመበርበር ዋንጫውን በጥንቃቄ ፈለገ፤ በመጨረሻ ግን ዋንጫው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ።

13 ወንድማማቾቹ ይህን ባዩ ጊዜ በሐዘን ልብሶቻቸውን ቀደዱ፤ ስልቻዎቻቸውንም ጭነው ወደ ከተማ ተመለሱ።

14 ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ሲመጡ ገና በቤት ሳለ አገኙት፤ ወደ መሬት ጐንበስ ብለው እጅ ነሡት፤

15 ዮሴፍም “ይህ ያደረጋችኹት ነገር ምንድን ነው? እኔ ባለሁበት ደረጃ የሚገኝ ሰው በተለየ ጥበብ ሁሉን ነገር መርምሮ ማወቅ የማይችል መሰላችሁን?”

16 ይሁዳም “እንግዲህ ለጌታችን ምን መልስ እንሰጣለን? ራሳችንን ነጻ የምናደርግበት መልስ መስጠት ከቶ አንችልም፤ እግዚአብሔር የሠራነውን በደል ገልጦታል፤ እንግዲህ ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሪያዎችህ እንሁን” አለ።

17 ዮሴፍም “ይህንንስ ከቶ አላደርገውም! ዋንጫው የተገኘበት ሰው ብቻ የእኔ ባሪያ መሆን አለበት፤ ሌሎቻችሁ በሰላም ወደ አባታችሁ መመለስ ትችላላችሁ!” አለ።


ይሁዳ ስለ ብንያም ዮሴፍን መለመኑ

18 ይሁዳ ወደ ዮሴፍ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ፤ እባክህ አንድ ቃል እንድናገር ፍቀድልኝ፤ ምንም እንኳ የፈርዖንን ያኽል የተከበርክ ብትሆን እባክህ አትቈጣኝ።

19 ጌታዬ ከአሁን ቀደም ‘አባት አላችሁ ወይ? ሌላ ወንድምስ አላችሁ ወይ?’ ብለህ ጠየቅከን፤

20 እኛም ‘ሽማግሌ አባት አለን፤ በስተርጅና የወለደውም ታናሽ ወንድም አለን፤ የልጁ ወንድም ሞቶአል፤ ከእናቱ ልጆች የቀረው እርሱ ብቻ ስለ ሆነ አባቱ በጣም ይወደዋል’ ብለንህ ነበር፤

21 አንተም ‘አየው ዘንድ ይዛችሁልኝ እንድትመጡ’ አልከን፤

22 እኛም ‘ልጁ አባቱን ትቶ መምጣት አይችልም፤ ትቶ ከመጣ ግን አባትየው መሞቱ የማይቀር ነው’ ብለን ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ ነበር።

23 ጌታችንም ለአንተ ለጌታችን ነግረንህ አገልጋዮቹን ‘ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ በፊቴ አትቀርቡም’ ብለህ በብርቱ አስጠነቀቅከን።

24 “እኛም ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜ ያልከንን ሁሉ ነገርነው፤

25 ከዚህ በኋላ እርሱ ‘አሁንም ወደ ግብጽ ተመለሱና ጥቂት እህል ሸምቱልን’ አለን።

26 እኛም ‘ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር ካልሆነ በሰውየው ፊት መቅረብ አንችልም፤ ስለዚህ ወደዚያ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ከእኛ ጋር የሄደ እንደሆን ብቻ ነው’ አልነው።

27 አባታችንም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ራሔል ሁለት ወንዶች ልጆች ብቻ እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ።

28 ከእነርሱ አንዱ ከአሁን በፊት ተለይቶኛል፤ ከተለየኝ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስላላየሁት ክፉ አውሬ በልቶት ይሆናል፤

29 አሁን ደግሞ ይህንን ወስዳችሁ በእርሱ ላይ አደጋ ቢደርስበት በእርጅናዬ ዘመን የምታመጡብኝ ሐዘን ወደ መቃብር ያወርደኛል።’

30 “አሁንም ብላቴናው ከእኛ ተለይቶ በመቅረት ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብንመለስ የብላቴናው ነፍስ ከእርሱ ጋር የታሰረች ስለ ሆነ፥

31 ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ሲያይ ይሞታል፤ እኛ አገልጋዮችህም የአገልጋይህን የአባታችንን ሽበት በሐዘን ወደ መቃብር እናወርዳለን፤

32 ከዚህም በላይ ስለ ልጁ ደኅንነት ራሴን ዋስ አድርጌ ለአባቴ ሰጥቼአለሁ፤ ደግሞም ‘ልጁን በደኅና መልሼ ባላመጣው በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ተወቃሽ ልሁን’ ብዬ ቃል ገብቼለታለሁ።

33 “ስለዚህ እኔ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ፥

34 ልጁን ሳልይዝ እንዴት ወደ አባቴ መመለስ እችላለሁ? ይህን የመሰለ ከባድ ሥቃይ በአባቴ ላይ ሲደርስ ማየት አልችልም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos