ዘፍጥረት 20:3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ነገር ግን አንድ ሌሊት እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ አቤሜሌክን “ይህች ሴት ባለባል ስለ ሆነች እርስዋን በመውሰድህ ምክንያት ትሞታለህ” አለው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔርም በአንድ ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ፣ “እነሆ፤ በወሰድሃት ሴት ምክንያት ምዉት ነህ፤ እርሷ ባለባል ናት” አለው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ “እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ትሞታለህ፤ እርሷ ባለ ባል ናትና” አለው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያች ሌሊትም አቤሜሌክ ተኝቶ ሳለ እግዚአብሔር በሕልም ወደ እርሱ መጣ፤ እንዲህም አለው፥ “እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ትሞታለህ፤ እርስዋ ባለ ባል ናትና።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ እንዲህም አለው፤ እነሆ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ምውት ነህ እርስዋ ባለ ባል ናትና። |
ከዚህ በኋላ ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው? ሣራይ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርከኝም?
አሁን ግን ሴቲቱን ለባልዋ መልሰህ ስጥ፤ እርሱ ነቢይ ስለ ሆነ እንዳትሞት ይጸልይልሃል፤ እርስዋን መልሰህ ባትሰጥ ግን እንደምትሞት ዕወቅ፤ አንተ ብቻ ሳትሆን ሕዝብህም በሙሉ ታልቃላችሁ።”
ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ሌላ ሕልም አይቶ ወንድሞቹን “እነሆ፥ ሌላ ሕልም አየሁ፤ በሕልሜም ፀሐይ፥ ጨረቃና ዐሥራ አንድ ከዋክብት ሰገዱልኝ” አላቸው።
የንጉሡ የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ሁለቱም በእስር ቤት ሳሉ በአንድ ሌሊት ሕልም አዩ፤ የእያንዳንዳቸው ሕልም የተለያየ ትርጒም ነበረው።
እነርሱም “እያንዳንዳችን ሕልም አየን፤ ነገር ግን የእያንዳንዳችንን ሕልም የሚተረጒም ማንም የለም” አሉት። ዮሴፍም “ሕልም የመተርጐም ችሎታ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
ነገር ግን ይህን ነገር ሲያስብ ሳለ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ።
ከዚህም በላይ ጲላጦስ በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ፦ “በእርሱ ምክንያት ዛሬ ሌሊት በሕልም ብዙ ተሠቃይቻለሁና በዚያ በንጹሕ ሰው ላይ ምንም እንዳታደርግ” ስትል ላከችበት።