ዘኍል 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምባላቅ እስራኤልን እንዲረግምለት በለዓምን ማስጠራቱ 1 እስራኤላውያን ጒዞአቸውን በመቀጠል ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅና በኢያሪኮ ትይዩ በሚገኘው በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፈሩ። 2 የሞአብ ንጉሥ የጺጶር ልጅ ባላቅ እስራኤላውያን በአሞራውያን ላይ ያደረሱትን ጒዳት አየ፥ 3 በእስራኤላውያን ብዛት ምክንያት የሞአብ ሕዝብ ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው፤ እስራኤላውያንንም በጣም ፈሩ። 4 ሞአባውያን ለምድያማውያን ሽማግሌዎች “ይህ የምታዩት የሕዝብ ብዛት በሬ በመስክ የሚገኘውን ሣር ሁሉ ጠራርጎ እንደሚበላ በዙሪያችን ያለውን ነገር ሁሉ ጠራርጎ የሚያጠፋ ነው” አሉአቸው። ስለዚህ በዚያን ጊዜ የሞአብ ንጉሥ የነበረው የጺጶር ልጅ ባላቅ፥ 5 በዓማው ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በፐቶር ከተማ ይኖር ወደነበረው ወደ ቢዖር ልጅ ወደ በለዓም ይጠሩት ዘንድ መልእክተኞች እንዲህ ብሎ ላከበት፤ “ከግብጽ የወጣ አንድ ሕዝብ ምድሪቱን ሁሉ ሸፍኖአታል፤ እነርሱም በአቅራቢያችን ሰፍረዋል፤ 6 የሕዝቡም ቊጥር ከእኛ እጅግ የበዛ ነው፤ ስለዚህ ወደዚህ መጥተህ እነርሱን ርገምልኝ፤ በዚህ ዐይነት ምናልባት ድል ልነሣቸውና ከምድሪቱ ላስወጣቸው እችል ይሆናል፤ አንተ የምትመርቀው የተመረቀ፥ አንተም የምትረግመው የተረገመ እንደሚሆን ዐውቃለሁ።” 7 ስለዚህ የሞአባውያንና የምድያማውያን ሽማግሌዎች ስለ ርግማን የሚከፈለውን ገንዘብ ይዘው ወደ በለዓም በመሄድ የባላቅን መልእክት ሰጡት፤ 8 በለዓምም “እዚሁ ዕደሩና ነገ ጧት እግዚአብሔር የሚነግረኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ” አላቸው፤ በዚህ ዐይነት የሞአባውያን መሪዎች ከበለዓም ጋር ቈዩ። 9 እግዚአብሔርም ወደ በለዓም መጥቶ “እነዚህ ከአንተ ጋር ያሉት ሰዎች እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀው። 10 እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የሞአብ ንጉሥ የጲዖር ልጅ ባላቅ እንዲህ ብሎ ወደ እኔ የላካቸው ናቸው፦ 11 ‘ከግብጽ የወጣ ሕዝብ ምድሪቱን ሸፍኖአታል፤ መጥተህ ብትረግምልኝ ምናልባት እነርሱን በጦርነት ተዋግቼ ላስወጣቸው እችል ይሆናል።’ ” 12 እግዚአብሔርም በለዓምን “ከነዚህ ሰዎች ጋር አትሂድ፤ የተባረኩ ስለ ሆነ የእስራኤልን ሕዝብ አትርገም” አለው። 13 በለዓምም በማግስቱ ጠዋት ሲነጋ ተነሥቶ፥ ለባላቅ ሹማምንት “እንግዲህ ወደ ቤታችሁ ተመለሱ፤ እኔ ከእናንተ ጋር እንዳልሄድ እግዚአብሔር ከልክሎኛል” አላቸው፤ 14 ስለዚህ የሞአብ ሹማምንት ወደ ባላቅ ተመለሱና በለዓም አብሮአቸው ለመምጣት እምቢ እንዳለ ነገሩት። 15 ከዚያን በኋላ ባላቅ ከፊተኞቹ መልእክተኞች ይበልጥ የተከበሩና ቊጥራቸውም የበዛ ሹማምንት ወደ በለዓም ላከ፤ 16 እነርሱም ወደ በለዓም ሄደው የባላቅን መልእክት እንዲህ ሲሉ ነገሩት፤ “ወደ እኔ መምጣት እንዳትችል የሚያግድህ ነገር አይኑር! 17 ከፍ ባለ ክብር አከብርሃለሁ፤ የጠየቅከኝንም ሁሉ አደርግልሃለሁ፤ ስለዚህ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ ርገምልኝ።” 18 በለዓም ግን ለመልእክተኞቹ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ፤ “ባላቅ በቤተ መንግሥቱ የሚገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ ቢሰጠኝም በትንሽ ወይም በትልቅ ነገር የአምላኬን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ አይቻለኝም፤ 19 ነገር ግን እግዚአብሔር የሚነግረኝ ሌላ ነገር ካለ ከእርሱ እረዳ ዘንድ እስቲ እናንተም እንደ ፊተኞቹ መልእክተኞች ሌሊቱን እዚሁ አሳልፉ።” 20 በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ወደ በለዓም መጣና “እነዚህ ሰዎች ወደ አንተ የመጡት ይዘውህ ሊሄዱ ከሆነ ተነሥተህ አብረሃቸው ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ አድርግ” አለው። 21 ስለዚህ በማግስቱ ጠዋት በለዓም ተነሣና አህያውን ጭኖ ከሞአባውያን መሪዎች ጋር ሄደ። በለዓምና አህያይቱ 22 በለዓም በመሄዱ እግዚአብሔር ተቈጣ፤ በለዓም ሁለቱን አሽከሮቹን በማስከተል በአህያው ላይ ተቀምጦ በሚጓዝበት ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በፊቱ ቆሞ መንገዱን ዘጋበት፤ 23 መልአኩ ሰይፉን መዞ በመንገዱ ላይ መቆሙን አህያይቱ በተመለከተች ጊዜ መንገዱን ለቃ ወደ እርሻ ገባች፤ በለዓምም አህያይቱን ወደ መንገዱ ለመመለስ ደበደባት፤ 24 መንገዱ በሁለት የወይን ተክል ቦታዎች መካከል እየጠበበ ሲሄድና በሁለቱም በኩል የድንጋይ ግንብ ሲገጥመው መልአኩ መጥቶ በፊት ለፊት ቆመ። 25 አህያይቱ መልአኩን ባየች ጊዜ ወደ ግንቡ ተጠግታ የበለዓምን እግር ከግንቡ ጋር አጣበቀችው፤ በለዓም አሁንም አህያይቱን መደብደብ ጀመረ፤ 26 እንደገናም መልአኩ ወደ ፊት ቀድሞ ሄደና በግራም ሆነ በቀኝ መተላለፊያ በሌለበት ጠባብ ቦታ ላይ ቆመ። 27 በዚህን ጊዜ አህያይቱ መልአኩን ስታይ በመሬት ላይ ተኛች፤ በለዓምም እጅግ ተቈጥቶ አህያይቱን በብትር መደብደብ ጀመረ። 28 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ለአህያይቱ የመናገር ችሎታ ስለ ሰጣት በለዓምን “እኔ ምን አደረግሁህ? ሦስት ጊዜ የደበደብከኝ ስለምንድን ነው?” አለችው። 29 በለዓምም “እጅግ ስለ ተጫወትሽብኝ ነዋ! ሰይፍ ቢኖረኝማ አሁን በገደልኩሽ ነበር!” አላት። 30 አህያይቱም “በሕይወትህ ሙሉ ስትጋልበኝ የኖርክ አህያህ አይደለሁምን? ታዲያ ከዚህ በፊት እንደ ዛሬ ሆኜብህ ዐውቃለሁን?” ስትል መለሰችለት። በለዓምም “ከቶ እንዲህ ሆነሽብኝ አታውቂም” አላት። 31 በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በለዓም ሰይፍ ይዞ የቆመውን መልአክ ለማየት እንዲችል አደረገው፤ በለዓምም በግንባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ 32 መልአኩም እንዲህ አለው፤ “አህያህን እንዲህ አድርገህ ሦስት ጊዜ የመታሃት ለምንድን ነው? እኔ መጥቼ መንገድህን የዘጋሁት በጥፋት ጐዳና እንዳትሄድ ልከለክልህ ብዬ ነው፤ 33 የአንተ አህያ ግን እኔን በማየትዋ ሦስት ጊዜ ከፊቴ ሸሸች፤ አህያይቱ እንዲህ ባታደርግ ኖሮ አንተን ገድዬ እርስዋ በሕይወት እንድትኖር በተውኳት ነበር።” 34 በለዓምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በእርግጥ ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ አንተ እኔን ለመቃወም በመንገድ ላይ መቆምህን አላወቅሁም ነበር፤ አሁንም ወደዚያ መሄዴ ስሕተት መስሎ ከታየህ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ።” 35 መልአኩ ግን “ከእነዚህ ሰዎች ጋር መሄዱን ሂድ፤ ነገር ግን እኔ የምነግርህን ብቻ ተናገር” አለው፤ በዚህ ዐይነት በለዓም ከባላቅ ባለሥልጣኖች ጋር ሄደ። ባላቅ በለዓምን በደስታ እንደ ተቀበለው 36 ባላቅ የበለዓምን መምጣት በሰማ ጊዜ እርሱን ለመቀበል በሞአብ ጠረፍ በአርኖን ወንዝ ዳር ወደምትገኘው ወደ ዔር ከተማ ሄደ። 37 ባላቅ በለዓምን “በመጀመሪያ ሰዎች በላክሁብህ ጊዜ ስለምን አልመጣህም? አንተን ለማክበር የማልችል መስሎህ ነውን?” ሲል ጠየቀው። 38 በለዓምም “ያም ሆነ ይህ አሁን መጥቼ የለምን? ታዲያ አሁንስ ቢሆን በራሴ ምን ኀይል አለኝ? እኔ ልናገር የምችለው እግዚአብሔር የሚነግረኝን ብቻ ነው” ሲል መለሰለት። 39 ስለዚህ በለዓም ከባላቅ ጋር ወደ ቂርያት ሑጾት ከተማ ሄደ። 40 በዚያም ባላቅ፥ ከብቶችና በጎች አሳርዶ ከሥጋው ጥቂቱን አብረውት ለነበሩት መሪዎችና ለበለዓም ሰጠ። 41 በማግስቱ ጠዋት ባላቅ በለዓምን የእስራኤልን ሕዝብ በከፊል ለማየት ወደሚቻልበት ወደ ባሞትበዓል አወጣው። |