ዘፍጥረት 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)አብርሃም በገራር 1 አብርሃምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ምድር ሄደ፥ በቃዴስና በሹር መካከልም ተቀመጠ፥ በገራርም በእንግድነት በተቀመጠበት ጊዜ፥ 2 አብርሃም ሚስቱን ሣራን፦ “እኅቴ ናት” አለ፥ የገራርም ንጉሥ አቢሜሌክ በመልክተኛ ሣራን ወሰዳት። 3 እግዚአብሔርም ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጣ፥ “እነሆ፥ አንተ ስለ ወሰድሃት ሴት ትሞታለህ፤ እርሷ ባለ ባል ናትና” አለው። 4 አቢሜሌክ ግን አልቀረባትም ነበር፥ እሱም እንዲህ አለ፦ “አቤቱ፥ ጻድቁን ሕዝብ ደግሞ ታጠፋለህን? 5 ‘እኅቴ ናት’ ያለኝ እርሱ አይደለምን? እርሷም ደግሞ ራስዋ፥ ‘ወንድሜ ነው’ ብላኛለች፥ ይህንን በቅን ልብ እና በንጹሕ ኅሊና ነው ያደረግሁት”። 6 እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው፦ “ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፥ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውኩህም። 7 አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፥ እርሱ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንደምትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንደሚጠፋ በእርግጥ እወቅ።” 8 አቢሜሌክም በነገታው ማልዶ ተነሣ፥ ባለሟሎቹንም ሁሉ ጠርቶ የሆነውን ነገር ሁሉ ነገራቸው፥ ሰዎቹም እጅግ ደነገጡ። 9 አቢሜሌክም አብርሃምን ጠርቶ አለው፦ “ይህ ያደረግህብን ምንድነው? ምንስ ክፉ ሠራሁብህ? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ትልቅ ኃጢአት ያመጣህብን ምን ብንበድልህ ነው? ፈጽሞ የማይገባ ነገር በእኔ ፈጸምክብኝ።” 10 አቢሜሌክም አብርሃምን አለው፦ ይህን ማድረግህ ምን አይተህ ነው? 11 አብርሃምም አለ፦ “በዚህ ስፍራ እግዚአብሔርን መፍራት በእውነት እንደሌለ፥ ለሚስቴም ሲሉ እንደሚገድሉኝ ስላሰብሁ ነው። 12 እርሷም ደግሞ በእውነት እኅቴ ናት፥ የእናቴ ልጅ አይደለችም እንጂ የአባቴ ልጅ ናት፥ ለእኔም ሚስት ሆነች። 13 እግዚአብሔርም ከአባቴ ቤት ባወጣኝ ጊዜ አልኋት፦ ‘በገባንበት አገር ሁሉ ለእኔ የምታደርጊው ወሮታ ይህ ነው፦ ወንድሜ ነው ብለሽ ስለ እኔ ተናገሪ።’” 14 አቢሜሌክም በጎችንና ላሞችን ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችን አመጣ፥ ለአብርሃምም ሰጠው፥ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15 አቢሜሌክም፦ “እነሆ፥ ምድሬ በፊትህ ናት፥ በወደድኸው ተቀመጥ አለ። 16 ሣራንም አላት፦ እነሆ፥ ለወንድምሽ ሺህ ሚዛን ብር ሰጠሁት፥ ያም እነሆ ከአንቺ ጋር ባሉት ሁሉ ፊት የዐይኖች መሸፈኛ ይሁንሽ፥ ጽድቅሽ ለሰዎች ሁሉ ተገልጦአልና።” 17 አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፥ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባርያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፥ 18 ጌታ በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት በአቢሜሌክ ቤት ማኅፀኖችን ሁሉ በፍጹም ዘግቶ ነበርና። |