Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አብርሃምና አቤሜሌክ

1 አብርሃም በመምሬ የነበረውን መኖሪያውን ለቆ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ በቃዴስና በሹር መካከልም ተቀመጠ፤ በገራርም በእንግድነት በተቀመጠበት ጊዜ፥

2 አብርሃም ሚስቱን ሣራን እኅቴ ናት አለ፤ ስለዚህ የገራራ ንጉሥ አቤሜሌክ ሰዎች ልኮ ሣራን እንዲያመጡለት አደረገ።

3 ነገር ግን አንድ ሌሊት እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ አቤሜሌክን “ይህች ሴት ባለባል ስለ ሆነች እርስዋን በመውሰድህ ምክንያት ትሞታለህ” አለው።

4 ሆኖም አቤሜሌክ ገና ወደ እርስዋ አልቀረበም ነበርና እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! እኔ ምንም በደል አልፈጸምኩም፤ ታዲያ እኔንና ሕዝቤን ታጠፋለህ

5 እኅቴ ነች ያለኝ ራሱ አብርሃም ነው፤ እርስዋም ወንድሜ ነው ብላኛለች፤ እኔ ይህን ያደረግኹት በቅንነትና በንጹሕ ኅሊና ስለ ሆነ ምንም በደል አልፈጸምኩም” አለ።

6 እግዚአብሔርም በሕልም እንዲህ አለው፦ “በንጹሕ ኅሊና እንዳደረግህ ዐውቄአለሁ፤ ወደ እርስዋ ቀርበህ በእኔ ፊት ኃጢአት እንዳትሠራ ያደረግኩህም ስለዚህ ነው።

7 አሁን ግን ሴቲቱን ለባልዋ መልሰህ ስጥ፤ እርሱ ነቢይ ስለ ሆነ እንዳትሞት ይጸልይልሃል፤ እርስዋን መልሰህ ባትሰጥ ግን እንደምትሞት ዕወቅ፤ አንተ ብቻ ሳትሆን ሕዝብህም በሙሉ ታልቃላችሁ።”

8 በማግስቱ ጠዋት በማለዳ አቤሜሌክ ባለሟሎቹን ጠርቶ የሆነውን ነገር ሁሉ በተረከላቸው ጊዜ ደነገጡ።

9 ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ አብርሃምን ጠርቶ፦ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? በእኔና በመንግሥቴ ላይ ይህን በደል ያመጣህብን ምን ያስቀየምኩህ ነገር ቢኖር ነው? አንተ ያደረግህብኝን ነገር ከቶ ማንም ሰው አያደርገውም፤

10 ለመሆኑ ይህን ያደረግኸው ለምንድን ነው?”

11 አብርሃምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ ‘እዚህ ቦታ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የለም’ ብዬ በማሰብ ‘ሚስቴን ለመውሰድ በመፈለግ ይገድሉኛል’ ብዬ ስለ ሰጋሁ ነው፤

12 ደግሞም እርስዋ የአባቴ ልጅ ስለ ሆነች በእርግጥ እኅቴ ናት፤ ነገር ግን የእናቴ ልጅ ስላልሆነች አገባኋት።

13 ስለዚህ እግዚአብሔር ከአባቴ ቤት ወጥቼ ወደ ባዕድ አገር እንድሄድ ባዘዘኝ ጊዜ ‘በምንሄድበት ቦታ ሁሉ እኅቱ ነኝ ብትዪ ለእኔ ታላቅ ውለታ እንዳደረግሽልኝ እቈጥረዋለሁ’ ብዬአት ነበር።”

14 ከዚህ በኋላ አቤሜሌክ ሣራን ለአብርሃም መልሶ ሰጠው፤ እንዲሁም በጎችና በሬዎች የወንድና የሴት አገልጋዮችም ሰጠው።

15 አብርሃምን “እነሆ የእኔ ግዛት በፊትህ ነው፤ በፈለግከው ስፍራ ኑር” አለው።

16 ሣራንም “አንቺ ምንም አስነዋሪ ተግባር ያልፈጸምሽ ንጹሕ መሆንሽን ከአንቺ ጋር ያሉት ሰዎች ሁሉ እንዲረዱት ምልክት ይሆን ዘንድ ለወንድምሽ ለአብርሃም አንድ ሺህ ብር ሰጥቼዋለሁ” አላት።

17 ከዚያ በኋላ አብርሃም ለእግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቤሜሌክንና ሚስቱን፥ ሴቶች አገልጋዮቹንም ፈውሶአቸው ልጆች እንዲወልዱ አድርጎአቸዋል፤

18 በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት የአቤሜሌክ ቤተሰብን ማሕፀን ሁሉ ዘግቶ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos