Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 40 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዮሴፍ የእስረኞቹን ሕልም መተርጐሙ

1 ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ንጉሡን የሚያሳዝን በደል ፈጸሙ።

2 ፈርዖን በወይን ጠጅ አሳላፊውና በእንጀራ ቤት ኀላፊው እጅግ ተቈጣ።

3 ስለዚህ ዮሴፍ ታስሮ ወደሚገኝበት ወደ ዘበኞች አለቃ ቤት ተወስደው እንዲታሰሩ አደረገ።

4 የእስር ቤቱም አዛዥ ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም ያገለግላቸው ነበር። በእስር ቤትም ለጥቂት ጊዜ ቈዩ።

5 የንጉሡ የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ሁለቱም በእስር ቤት ሳሉ በአንድ ሌሊት ሕልም አዩ፤ የእያንዳንዳቸው ሕልም የተለያየ ትርጒም ነበረው።

6 በማግስቱ ጠዋት ዮሴፍ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል በገባ ጊዜ ተክዘው አገኛቸውና፥

7 “ዛሬ በፊታችሁ ላይ ሐዘን የሚታየው ለምንድን ነው?” አላቸው።

8 እነርሱም “እያንዳንዳችን ሕልም አየን፤ ነገር ግን የእያንዳንዳችንን ሕልም የሚተረጒም ማንም የለም” አሉት። ዮሴፍም “ሕልም የመተርጐም ችሎታ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።

9 የወይን ጠጅ አሳላፊው እንዲህ በማለት ሕልሙን ተናገረ፤ “በሕልሜ አንድ የወይን ተክል አየሁ፤

10 በተክሉም ላይ ሦስት ሐረጎች ነበሩ፤ ቅጠሉ ለምልሞ ወዲያው አበባ አወጣ፤ የወይን ዘለላውም ወዲያው በሰለ፤

11 የፈርዖን ጽዋ በእጄ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ወስጄ በጽዋው ውስጥ ጨመኩና ጽዋውን ለፈርዖን ሰጠሁት።”

12 ዮሴፍም እንዲህ አለ፤ “የሕልሙ ትርጕም ይህ ነው፤ ሦስቱ የወይን ሐረጎች ሦስት ቀኖች ናቸው፤

13 በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ንጉሡ ከእስራት ይፈታሃል፤ በደልህንም ይቅር ብሎ ወደ ቀድሞው ማዕርግህ ይመልስሃል፤ ቀድሞ የመጠጥ ቤት ኀላፊ ሆነህ ታደርገው እንደ ነበር የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ።

14 ነገር ግን ሁሉ ነገር በተቃናልህ ጊዜ እኔን አስታውሰህ እርዳኝ፤ ለፈርዖንም አሳስበህ ከእዚህ ከእስር ቤት እንድወጣ አድርገኝ።

15 እኔ ከዕብራውያን አገር ወደዚህ የመጣሁት ወድጄ ሳይሆን ተሸጬ ነው፤ እዚህም አገር ከመጣሁ ወዲህ በእስር ቤት የምገኘው ምንም በደል ሳልፈጽም ነው።”

16 የእንጀራ ቤት ኀላፊውም ዮሴፍ ለወይን ጠጅ አሳላፊው ሕልም የሰጠው ትርጒም መልካም መሆኑን ባየ ጊዜ፥ የእርሱንም ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ብሎ ነገረው፤ “እኔም በበኩሌ ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ ‘ሦስት መሶብ እንጀራ በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤

17 ከሁሉ በላይ ባለው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ ልዩ ልዩ ምግብ ነበረበት፤ ነገር ግን ወፎች ምግቡን ከመሶቡ እያነሡ ይበሉት ነበር።’ ”

18 ዮሴፍም “የሕልሙ ትርጒም እንዲህ ነው፤ ሦስት መሶቦች ሦስት ቀኖች ናቸው፤

19 በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ፈርዖን ከዚህ እስር ቤት አውጥቶ ራስህን ካስቈረጠ በኋላ በእንጨት ላይ ያሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።”

20 በሦስተኛው ቀን የፈርዖን ልደት በዓል ስለ ነበረ ለመኳንንቱ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ በዚያኑ ቀን የወይን ጠጅ አሳላፊውና የእንጀራ ቤት ኀላፊው ከእስር ቤት ወጥተው በመኳንንቱ ፊት እንዲቀርቡ አደረገ።

21 የወይን ጠጅ አሳላፊውን ወደ ቀድሞ ማዕርጉ መለሰው፤ ስለዚህ የወይን ጠጅ ጽዋውን ለንጉሡ መስጠት ጀመረ።

22 የእንጀራ ቤት ኀላፊውን ግን እንዲሰቀል አደረገው፤ ሁሉም ነገር ዮሴፍ የእያንዳንዳቸውን ሕልም እንደ ተረጐመው ሆነ።

23 የወይን ጠጅ አሳላፊው ግን ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ስለ ዮሴፍ የሆነውን ሁሉ ረሳ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos