ሶፎንያስ 3:20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያ ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ በሰበሰብኳችሁም ጊዜ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል ጌታ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያ ጊዜ እሰበስባችኋለሁ፤ ያን ጊዜ ወደ አገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ዐይናችሁ እያየ፣ ምርኳችሁን በምመልስበት ጊዜ፣ መከበርንና መወደስን፣ በምድር ሕዝብ ሁሉ መካከል እሰጣችኋለሁ”፤ ይላል እግዚአብሔር። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ሰብስቤ ወደ ሀገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ንብረታችሁን ሁሉ ዐይናችሁ እያየ በምመልስላችሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ዝነኞችና የተመሰገናችሁ ትሆናላችሁ።” የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፣ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፥ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። |
ከእናንተም ዘንድ ታገኙኛላችሁ፥ ይላል ጌታ፤ ምርኮአችሁንም እመልሳለሁ፥ ከአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እናንተንም ካሳደድሁበት ስፍራ ሁሉ እሰበስባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ፤ እናንተንም ለምርኮ ካፈለስሁበት ስፍራ እመልሳችኋለሁ።
እነሆ፥ የሕዝቤን የእስራኤልንና የይሁዳን ምርኮ የምመልስበት ዘመን ይመጣልና፥ ይላል ጌታ፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠኋት ምድር እመልሳቸዋለሁ፥ እነርሱም ይወርሱአታል፥ ይላል ጌታ።”
የምሠራላቸውንም በጎነት ሁሉ በሚሰሙ የምድር አሕዛብ ሁሉ ፊት ይህች ከተማ ለእኔ የምስጋናና የክብር የደስታም ስም ትሆናለች፤ እኔም ስላደረግሁላት በጎነትና ሰላም ሁሉ ይፈራሉ ይንቀጠቀጣሉም።
ምርኮአቸውን እመልሳለሁ፤ የሰዶምና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ የሰማርያንና የሴቶች ልጆችዋን ምርኮ፥ በመካከላቸው ያለውን የአንቺንም ምርኮ እመልሳለሁ፥
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ በሰበሰብሁ ጊዜ፥ በአሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ ለባርያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ።
የጠፋውን እፈልጋለሁ፥ የባዘነውን እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን አጠፋለሁ፤ በፍትሕም እጠብቀዋለሁ።
ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ፥ እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፥ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣችኋለሁ።
አንተም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የእስራኤልን ልጆች ከሄዱባቸው ሕዝቦች መካከል እወስዳለሁ፥ ከየስፍራውም እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም አመጣቸዋለሁ።
እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ በአሕዛብ እንዲማረኩ አድርጌአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና፥ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አላስቀርም።
የሕዝቤን የእስራኤልን ምርኮ እመልሳለሁ፥ የፈረሱትንም ከተሞች ዳግም ሠርተው ይቀመጡባቸዋል፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁንም ይጠጣሉ፤ የአትክልት ስፍራዎችንም ያበጃሉ፥ ፍሬውንም ይበላሉ።
ያዕቆብ ሆይ፥ ሁላችሁንም ፈጽሞ እሰበስባለሁ፥ የእስራኤልን ትሩፍ በአንድ ላይ እሰበስባለሁ፤ በጋጣ ውስጥ እንዳሉ በጎች፥ በማሰማርያው ውስጥ እንዳለ መንጋ አደርገዋለሁ፤ ከሰው ብዛት የተነሣ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ትሩፍ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ፤ ጌታ አምላካቸው ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳል።
እነሆ በዚያ ዘመን፥ ያስጨነቁሽን ሁሉ እቀጣለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።
የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ በረከት መሆን እንድትችሉ አድናችኋለሁ፤ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋናና በስም፥ በክብር ከፍ እንደሚያደርግህና እርሱም እንደ ተናገረ ለጌታ እግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ አደረገህ።”