ሕዝቅኤል 39 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የጎግ ሠራዊት መሸነፍ 1 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ አሁንም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሞሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፥ 2 እመልስሃለሁ፥ እመራሃለሁ፥ ከሰሜን ዳርቻ አወጣሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች እወስድሃለሁ። 3 ቀስትህን ከግራ እጅህ እመታለሁ፥ ፍላጻዎችህንም ከቀኝ እጅህ አስጥልሃለሁ። 4 አንተ፥ ወታደሮችህና ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ ሁሉ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። 5 አንተ በሜዳ ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6 በማጎግ እና ያለ ስጋት በደሴቶች በሚቀመጡት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 7 ቅዱሱ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል እንዲታወቅ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ እንዲሰደብ አልፈቅድም፤ አሕዛብም በእስራኤል ያለሁ ቅዱስ ጌታ እኔ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 8 እነሆ፥ ይመጣል ይሆናልም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያ ያልሁት ቀን ይህ ነው። 9 በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ወጥተው፥ የጦር መሣሪያዎችን፥ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትና ፍላጻዎችን፥ የእጅ በትሮችንና ጦርንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 10 በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከሜዳ አይሸከሙም፥ ከዱርም አይቆርጡም፤ የዘረፉአቸውን ይዘርፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጎግ ቀብር 11 በዚያም ቀን በእስራኤል፥ በባሕሩ በምሥራቅ በኩል ባለው በመንገደኞች ሸለቆ ለጎግ የመቃብር ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ስለሚቀበሩ፥ የመንገደኞች መተላለፊያ ይዘጋል፤ “የሐሞን-ጎግ ሸለቆ” ተብሎ ይጠራል። 12 የእስራኤል ቤት ምድሪቱን ለማጽዳት ሰባት ወር ሙሉ ይቀብሩአቸዋል። 13 የምድሪቱ ሕዝቦች ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፤ በምከበርበት ቀን፥ ለሥም ይሆንላቸዋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 ምድሪቱን ለማጽዳት በምድሪቱ ላይ ዘወትር የሚመላለሱና በምድር ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ ሰዎችን ይለያሉ፤ ከሰባቱ ወር በኋላ ፍለጋ ይጀምራሉ። 15 በምድርም የሚመላለሱት ሲያልፉ የሰው አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ በአጠገቡ ምልክት ያኖሩበታል። 16 ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። ምድሪቱንም ያጸዳሉ። 17 አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ፥ ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ኑ፥ ተሰብሰቡ፥ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕቴ፥ ወደ ታላቁ መሥዋዕት ከየስፍራው ተሰብሰቡ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ደምንም ትጠጣላችሁ። 18 የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ፥ የምድር አለቆችን፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሻንን ፍሪዳዎች ሁሉ ደም ትጠጣላችሁ። 19 እኔ በማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ፥ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። 20 በማእዴ ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ወደ ምድሪቱ መመለስ 21 ክብሬን ለአሕዛብ እሰጣለሁ፥ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን እና በላያቸው ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። 22 ከዚያች ቀን ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ። 23 የእስራኤል ቤት በበደላቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ አሕዛብ ያውቃሉ፤ እኔን ስለ በደሉኝ፥ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ። 24 እንደ ርኩሰታቸውና እንደ መተላለፋቸው መጠን አደርግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ። 25 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። 26 ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው በሰላም በተቀመጡ ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ይሸከማሉ። 27 ይህም የሚሆነው ከአሕዛብ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በእነሱ በተቀደስሁ ጊዜ ነው። 28 እኔ ጌታ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ፥ በአሕዛብ እንዲማረኩ አድርጌአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና፥ ከእነርሱ አንድ ሰው እንኳ በዚያ አላስቀርም። 29 ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሰውርም፥ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |