Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢሳይያስ 62 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪ ወጣ ድረስ፥ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም አላርፍም።

2 አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የጌታም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ።

3 በጌታ እጅ የውበት አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።

4 ከእንግዲህ ወዲህ፦ የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ፦ ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን ጌታ ደስታዬ ባንቺ ነው ብሏታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ፦ ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም፦ ባል ያገባች ትባላለች።

5 ጎልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል።

6 ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም። እናንት ወደ ጌታ አቤት፤ አቤት የምትሉ፤ ፈጽሞ አትረፉ፤

7 ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ለእርሱም ዕረፍት አትስጡት።

8 ጌታ፦ ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤

9 ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል ጌታንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሏል።

10 እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጎዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓርማ አሳዩ።

11 እነሆ፥ ጌታ ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል፦ ለጽዮን ልጅ፦ “እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር፥ ሥራውም በፊቱ አለ” በሏት።

12 “ጌታ የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም፥ “የተፈለገች፥ ያልተተወችም ከተማ” ትባያለሽ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos