Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሚክያስ 4 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


በመታዘዝ የሚመጣ ሰላምና መረጋጋት

1 እንዲህም ይሆናል፥ በመጨረሻው ዘመን የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶች በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።

2 ብዙዎች አሕዛብ መጥተው፦ ኑ ወደ ጌታ ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ እኛም በፍለጋው እንሄዳለን ይላሉ፤ ከጽዮን ሕግ፥ ከኢየሩሳሌምም የጌታ ቃል ይወጣልና።

3 በብዙዎች ሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፥ በሩቅም ባሉ በብርቱዎች መንግሥታት ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውን ወደ ማረሻ፥ ጦራቸውን ወደ ማጭድ ለመለወጥ ይቀጠቅጣሉ፤ መንግሥት በመንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም።

4 እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፥ የሚያስፈራውም የለም፤ የሠራዊት ጌታ አፍ ተናግሮአልና።

5 ሕዝብ ሁሉ እያንዳንዱ በየአምላኩ ስም ይሄዳልና፥ እኛ ግን በጌታ አምላካችን ስም ለዘለዓለም ዓለም እንሄዳለን።


ከስደት መልስ ለመታደስ የተገባላቸው ቃል

6 በዚያ ቀን ይላል ጌታ፥ አንካሳይቱን እሰበስባለሁ፥ የተጣለችውንና የጎዳኋትን አከማቻለሁ፤

7 አንካሳይቱን ትሩፍ፥ የተጣለችውን ብርቱ መንግሥት አደርጋታለሁ፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም በጽዮን ተራራ ጌታ በእነርሱ ላይ ይነግሣል።

8 አንተ የመንጋው ግንብ ሆይ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ምሽግ ሆይ፥ የቀደመችው ግዛት፥ የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ መንግሥት ወደ አንተ ትገባለች።

9 አሁንስ ለምን ጮክ ብልሽ ታለቅሻለሽ? በአንቺ ዘንድ ንጉሥ ስለ ሌለ ነውን? እንደምትወልድ ሴት ምጥ የያዘሽ፥ መካሪሽ ስለ ጠፋ ነውን?

10 የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እንደምትወልድ ሴት አምጪ፥ ተጨነቂ፤ አሁን ከከተማ ወጥተሽ በሜዳ ትቀመጫለሽና፥ ወደ ባቢሎንም ትሄጃለሽ፤ በዚያ ትድኛለሽ፥ በዚያም ጌታ ከጠላቶችሽ እጅ ይቤዥሻል።

11 አሁንም፦ “ትርከስ፥ ዓይናችን በጽዮን ላይ ይሁን” የሚሉ ብዙ አሕዛብ በአንቺ ላይ ተሰብስበዋል።

12 ነገር ግን የጌታን አሳብ አያውቁም፥ ምክሩንም አያስተውሉም፤ እንደ ነዶ በአውድማ አከማችቷቸዋልና።

13 የጽዮን ልጅ ሆይ ተነሺ አሂጂ፥ ቀንድሽን ብረት፥ ኮቴሽንም ናስ አደርጋለሁና፤ ብዙ ሕዝቦችን ታደቅቂአለሽ፤ እኔም ትርፋቸውን ለጌታ፥ ሀብታቸውንም ለምድር ሁሉ ጌታ አውለዋለሁ።

14 አሁንም የወታደሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ወታደሮችን ትሰበስቢያለሽ፥ በእኛ ላይ ከበባ አድርገዋል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጉንጩን በበትር ይመታሉ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos