ኤርምያስ 44:7 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ትሩፍ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ልጅንና ሕፃንን ከእናንተ ለማጥፋት ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? አዲሱ መደበኛ ትርጒም “አሁንም የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ዘር እንዳይቀርላችሁ ወንዶችና ሴቶች፣ ልጆችና ሕፃናት በይሁዳ እንዳይገኙ ለምን እንዲህ ዐይነት ታላቅ ጥፋት በራሳችሁ ላይ ታመጣላችሁ? አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም “አሁንም እኔ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እስቲ ልጠይቃችሁ፦ እናንተስ ራሳችሁ ለምን ይህን ሁሉ ክፉ ነገር ታደርጋላችሁ? ከይሁዳ ሕዝብ መካከል አንድ እንኳ ለዘር እንዳይተርፍ በወንዶችና በሴቶች፥ በልጆችና በሕፃናት ላይ ጥፋት እንዲመጣ ለምን ትፈልጋላችሁ? የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) “አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ቅሬታ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ብላቴናንና የሚጠባ ሕፃንን ከመካከላችሁ ታጠፉ ዘንድ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን ቅሬታ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ብላቴናንና ሕፃንን ከመካከላችሁ ታጠፉ ዘንድ ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? |
በውኑ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስና ሕዝቡ ሁሉ ገደሉትን? በውኑ ንጉሡ ጌታን አልፈራን? ወደ ጌታስ አልተማጠነምን? ጌታስ በእነርሱ ላይ የተናገረውን ክፉ ነገር አልተወምን? እኛም በነፍሳችን ላይ ታላቅ ክፋት እናደርጋለን።”
ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች በእርግጥ ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ።
እናንተ፦ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ ጌታ ጸልይ፥ ጌታ አምላካችንም የሚናገረውን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ ጌታ ወደ አምላካችሁ እናንተው ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል።
ስለዚህም በግብጽ ምድር በዚያ ለመቀመጥ ከገቡት ከይሁዳ ትሩፍ ማናቸውም ተመልሰው ለመቀመጠጥ ወደ ሚመኙበት ወደ ይሁዳ ምድር አያመልጡም በሕይወትም አይተርፉም አይመለሱምም፤ ከአንዳንድ ከሚያመልጡ በቀር አይመለሱም።”
እናንተም እንድትጠፉ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ እንድትሆኑ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት አጥናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ?
ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፥ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ።
ታው። እንደ በዓል ቀን የሚያስፈሩኝን ከዙሪያዬ ጠራህ፥ በእግዚአብሔር ቁጣ ቀንም ያመለጠ ወይም የቀረ አልተገኘም፥ ያቀማጠልኋቸውንና ያሳደግኋቸውን ጠላቴ በላቸው።
በሕያውነቴ እምላለሁ ኃጢአተኛው ሰው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ኃጢአተኛው እንዲሞት አልፈቅድም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ፥ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው።
ሽማግሌ፥ ወጣት፥ ድንግል፥ ሕፃናትንና ሴቶችን ግደሉ፥ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፥ በመቅደሴም ጀምሩ። በቤቱ ፊት ለፊት ከነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ።
በኃጢአታቸው የተነሣ ሕይወታቸውን አሳልፈው ለሞት የሰጡትን የእነዚያን ሰዎች ጥናዎች ጠፍጥፋችሁ ለመሠዊያ መለበጫ አድርጓቸው፤ በጌታ ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፥ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።”
አሁንም ሂድ፤ አማሌቃውያንን ውጋ፤ ያላቸውንም ሁሉ ፈጽመህ አጥፋ፤ አንዱንም አታስቀር፤ ወንዱንም ሴቱንም፥ ልጁንም ሕፃኑንም፥ የቀንድ ከብቱንም በጉንም፥ ግመሉንም አህያውንም ግደል።’ ”
የካህናቱንም ከተማ ኖብን በሰይፍ መታት፥ በዚያ የሚኖሩትንም ወንዶችንና ሴቶችን፥ ልጆችንና ጡት የሚጠቡ ሕፃናትን፥ እንዲሁም በሬዎችንና አህያዎችን፥ በጎችንም ሁሉ በሰይፍ ስለት አስገደለ።