Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ኢያሪኮ መያዝዋና መጥፋትዋ

1 ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ ፈጽማ ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርሷ የሚገባ ከእርሷም የሚወጣ ማንም አልነበረም።

2 ጌታም ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ተመልከት፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን ኃያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ።

3 እናንተም ከተማይቱን ትዞሩአታላችሁ፥ ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ ከተማይቱን በቀን አንድ ጊዜ ይዙሩአት፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ።

4 ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይሸከሙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።

5 ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማይቱም ቅጥር ይወድቃል፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ እርሷ አቅንቶ በቀጥታ ይገባል።”

6 የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የቃል ኪዳኑን ታቦት አንሱ፥ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በጌታ ታቦት ፊት ይሸከሙ።”

7 ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ሂዱ፥ ከተማይቱንም ዙሩ፥ ተዋጊዎቹም በጌታ ታቦት ፊት ይሂዱ።”

8 ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር።

9 ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።

10 ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።”

11 እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ።

12 ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ።

13 ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር።

14 በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ።

15 በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ።

16 በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ።

17 ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ።

18 እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም።

19 ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።”

20 ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት።

21 በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።

22 ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወደ አመንዝራይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ።”

23 ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው።

24 ከተማይቱንም በእርሷም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ ብቻ በጌታ ግምጃ ቤት አኖሩት።

25 ኢያሪኮንም ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርሷም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች።

26 በዚያን ጊዜም ኢያሱ እንዲህ ብሎ ማለ፦ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በጌታ ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ።”

27 ጌታም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ተሰማ።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos