ኤርምያስ 44 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ጣዖትን ማውገዝ 1 በግብጽ ምድር በሚግዶልና በጣፍናስ በሜምፎስም በጳትሮስም አገር ስለ ተቀመጡ አይሁድ ሁሉ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2 “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ከተሞች ሁሉ ያመጣሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ራሳችሁ አይታችኋል፤ እነሆ፥ ዛሬ ባድማ ሆነዋል፥ የሚቀመጥባቸውም የለም። 3 ይህም የሆነው ስለ ሠሩት ክፋት እኔን ስላስቈጡኝ፥ በዚህም እናንተም አባቶቻችሁም እነርሱም ለማያውቁአቸው ለሌሎች አማልክት ለማጠንና ለማገልገል ስለ ሄዱ ነው። 4 ሆኖም በማለዳ ተነሥቼ ባርያዎቼን ነቢያትን ሁሉ እንዲህ ብዬ ላክሁባችሁ፦ ‘እባካችሁ፥ እንደዚህ ያለ የጠላሁትን ርኩስ ነገር አታድርጉ።’ 5 ነገር ግን አልሰሙም ከክፋታቸውም ተመልሰው ለሌሎች አማልክት ላለማጠን ጆሮአቸውን አላዘነበሉም። 6 ስለዚህ መዓቴና ቁጣዬ ወረዱ፥ በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ነደዱ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ፈረሱ ባድማም ሆኑ። 7 አሁንም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ከይሁዳ ወገን መካከል ትሩፍ እንዳይቀርላችሁ፥ ወንድንና ሴትን፥ ልጅንና ሕፃንን ከእናንተ ለማጥፋት ይህን ታላቅ ክፋት በራሳችሁ ላይ ለምን ታደርጋላችሁ? 8 እናንተም እንድትጠፉ በምድርም አሕዛብ ሁሉ መካከል መረገሚያና መሰደቢያ እንድትሆኑ፥ ለመቀመጥ በገባችሁባት በግብጽ ምድር ለሌሎች አማልክት አጥናችሁ በእጃችሁ ሥራ ለምን ታስቈጡኛላችሁ? 9 በውኑ በይሁዳ ምድርና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያደረጉትን የአባቶቻችሁን ክፋት፥ የይሁዳንም ነገሥታት ክፋት፥ የሚስቶቻቸውንም ክፋት፥ የእናንተንም ክፋት፥ የሚስቶቻችሁንም ክፋት ረስታችሁታልን? 10 እስከ ዛሬ ድረስ አልተዋረዱም አልፈሩምም፥ በእናንተና በአባቶቻችሁም ፊት ባኖርሁት ሕጌና ሥርዓቴ አልሄዱም። 11 “ስለዚህም የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ይሁዳን ሁሉ ለማጥፋት ፊቴን ለክፋት በእናንተ ላይ አደርጋለሁ። 12 ወደ ግብጽም ለመግባት በዚያም ለመቀመጥ ፊታቸውን ያቀኑትን የይሁዳን ትሩፍ እወስዳለሁ፥ ሁሉም ይጠፋሉ፥ በግብጽም ምድር ይወድቃሉ፤ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ ከታናሹም ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ በሰይፍና በራብ ይሞታሉ፤ ለጥላቻና ለመሣቀቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ይሆናሉ። 13 ኢየሩሳሌምን በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንደ ቀጣሁ፥ እንዲሁ በግብጽ ምድር የሚኖሩትን እቀጣለሁ። 14 ስለዚህም በግብጽ ምድር በዚያ ለመቀመጥ ከገቡት ከይሁዳ ትሩፍ ማናቸውም ተመልሰው ለመቀመጠጥ ወደ ሚመኙበት ወደ ይሁዳ ምድር አያመልጡም በሕይወትም አይተርፉም አይመለሱምም፤ ከአንዳንድ ከሚያመልጡ በቀር አይመለሱም።” 15 ሚስቶቻቸውም ለሌሎች አማልክት ማጠናቸውን ያወቁ ሰዎች ሁሉ በዚያም ቆመው የነበሩ ሴቶች ሁሉ፥ በግብጽ ምድር በጳትሮስ የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ለኤርምያስ መለሱለት እንዲህም አሉ፦ 16 “አንተ በጌታ ስም የነገርኸንን ቃል አንሰማህም። 17 ነገር ግን እኛና አባቶቻችን ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ እንዳደረግነው፥ ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ ከአፋችን የወጣውን ቃል ሁሉ በእርግጥ እናደርጋለን፤ በዚያን ጊዜም እንጀራ እንጠግብ ነበር፥ መልካምም ይሆንልን ክፉም አናይም ነበር። 18 ለሰማይ ንግሥት ማጠንን ለእርሷም የመጠጥን ቁርባን ማፍሰስን ከተውን ወዲህ ግን፥ እኛ ሁሉ ነገር ጐድሎብናል፥ በሰይፍና በራብ አልቀናል። 19 እኛስ ለሰማይ ንግሥት ባጠንንላት የመጠጥንም ቁርባን ባፈሰስንላት ጊዜ፥ በውኑ ያለ ባሎቻችን ፈቃድ ምስልዋ ያለበት እንጐቻ አድርገንላታልን? የመጠጥንስ ቁርባን አፍስሰንላታልን?” 20 ኤርምያስም ይህን ቃል ለመለሱለት ሕዝብ ሁሉ፥ ለወንዶቹና ለሴቶቹ ለሕዝቡም ሁሉ፥ መለሰላቸው እንዲህም አለ፦ 21 “እናንተና አባቶቻችሁ ነገሥታቶቻችሁም አለቆቻችሁም የምድሪቱም ሕዝብ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ያጠናችሁትን ዕጣን ጌታ አያስታውሰውምን? በልቡስ አያኖረውምን? 22 ጌታም ከእንግዲህ ወዲህ የሥራችሁን ክፋትና ያደረጋችሁትን ርኩሰት መታገሥ አልቻለም፤ ስለዚህ ምድራችሁ ባድማ መሣቀቂያም መረገሚያም ሆናለች ዛሬም እንደሆነ የሚኖርባት የለም። 23 ስላጠናችሁ፥ በጌታም ላይ ኃጢአትን ስለ ሠራችሁ፥ የጌታንም ድምፅ ስላልሰማችሁ፥ በሕጉና በሥርዓቱም በምስክሩም ስላልሄዳችሁ፥ ስለዚህ ዛሬ እንደሆነ ይህ ክፉ ነገር ደርሶባችኋል።” 24 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ ለሴቶቹም ሁሉ እንዲህ አለ፦ “በግብጽ ምድር የምትገኙ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ። 25 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ እናንተና ሚስቶቻችሁ በአፋችሁ፦ ‘ለሰማይ ንግሥት ለማጠን የመጠጥንም ቁርባን ለእርሷ ለማፍሰስ የተሳልነውን ስእለታችንን በእርግጥ እንፈጽማለን’ ብላችሁ ተናገራችሁ በእጃችሁም አደረጋችሁት፤ እንግዲህ ስእለታችሁን አጽኑ ስእለታችሁንም ፈጽሙ። 26 ስለዚህ እናንተ በግብጽ ምድር የምትኖሩ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ስሙ፤ በግብጽ ምድር ሁሉ በሚኖር በይሁዳ ሰው ሁሉ አፍ ስሜ ከእንግዲህ ወዲህ፦ ‘ሕያው በሆነ ጌታ እግዚአብሔር እምላለሁ!’ ተብሎ እንዳይጠራ፥ እነሆ፥ በታላቅ ስሜ ምያለሁ፥ ይላል ጌታ። 27 እነሆ፥ ለመልካም ሳይሆን ለክፋት በእነርሱ ላይ እመለከታለሁ፤ በግብጽም ምድር ያሉት የይሁዳ ሰዎች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍና በራብ ያልቃሉ። 28 ከሰይፍም ያመለጡት ጥቂት ሰዎች ከግብጽ ምድር ወደ ይሁዳ ምድር ይመለሳሉ፤ በዚያም ለመቀመጥ ወደ ግብጽ ምድር የገቡት የይሁዳ ትሩፍ ሁሉ ከእኔ ወይም ከእነርሱ የማናችን ቃል እንደሚጸና በውኑ ያውቃሉ! 29 ቃሎቼም በእናንተ ላይ ለክፋት በእርግጥ እንደሚጸኑ እንድታውቁ በዚህች ስፍራ እቀጣችኋለሁ፤ ይህም ለእናንተ ምልክት ይሆናል፥ ይላል ጌታ። 30 ጌታ እንዲህ ይላል፦ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ጠላቱ ለሆነው ነፍሱንም ለሚሻው ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፥ እንዲሁ፥ እነሆ፥ የግብጹን ንጉሥ ፈርዖን ሖፍራን ለጠላቶቹ ነፍሱንም ለሚሽዋት እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ።” |