ዕንባቆም 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ለነቢዩ አቤቱታ መልስ 1 በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ ምን እንደሚለኝና በአቤቱታዬም ምን መልስ እንደምሰጥ ለማየት እጠባበቃለሁ። 2 ጌታም መለሰልኝ፥ እንዲህም አለ፦ ራእዩን ጻፍ፤ የሚያነበው እንዲሮጥ በጽላት ላይ በግልፅ አድርገው። 3 ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይፈጥናል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ጠብቀው፤ አይዘገይም። 4 እነሆ፥ እርሱ ኮርቶአል፥ ነፍሱ በውስጡ ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። 5 በእርግጥ ወይን አታላይ ነው፤ ትዕቢተኛ ሰው በስፍራው አርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል። የክፉ ሰው ኀዘን 6 እነዚህ ሁሉ፦ ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን? 7 አበዳሪዎችህ ድንገት አይነሡምን? የሚያንቀጠቅጡህ አይነቁምን? ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ። 8 አንተ ብዙ አሕዛብን በዝብዘሃልና፥ የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል። 9 ከክፉ ለመታደግ ጐጆውን በከፍታ ላይ በማድረግ፥ ለቤቱ ክፉ ትርፍን የሚሰበስብ ወዮለት! 10 ብዙ ሕዝቦችን ቆራርጠህ ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል። 11 ድንጋይ ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከወራጅ ይመልስለታል። 12 ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በበደል ለሚመሠርት ወዮለት! 13 እነሆ፥ አሕዛብ ለእሳት እንደሚሠሩ፥ ሕዝቦችም ለከንቱነት እንደሚደክሙ ከሠራዊት ጌታ ዘንድ የሆነ አይደለምን? 14 ውኃ ባሕርን እንደሚከድን፥ ምድር የጌታን ክብር በማወቅ ትሞላለችና። 15 ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት! 16 በክብር ፈንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጣ፥ እንዳልተገረዘም ተቆጠር፤ የጌታ የቀኙ ጽዋ በአንተ ላይ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። 17 ከሰው ደም፥ በምድሪቱ፥ በከተማይቱና በእርሷም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ከተደረገው ዓመጽ የተነሣ፤ በሊባኖስ ላይ የተደረገው ዓመጽ ይከድንሃል፤ የአራዊትም ጥፋት ያስፈራቸዋል። 18 ሠሪው የቀረጸውና ቀልጦ የተሠራ ምስል የውሸት አስተማሪ ነውና፤ ዲዳ ጣዖትን በመሥራት ሠሪው በሠራው ይታመናልና፤ የተቀረጸ ምስል ምን ይጠቅማል? 19 እንጨቱን “ንቃ” ዝም ያለውንም ድንጋይ “ተነሣ” ለሚለው ወዮለት! ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ በውስጡም ምንም እስትንፋስ የለበትም። 20 ጌታ ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድሪቷ ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል። |