ዘፀአት 14:25 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) የሰረገሎቹንም ጎማ አሰረ፥ ወደ ጭንቅም አስገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “ጌታ ግብፃውያንን ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔር የሠረገላዎቻቸውን መንኰራኲሮች ከመሬት ጋር ስላጣበቀባቸው ሠረገሎቻቸውን ነድተው ማንቀሳቀስ አልቻሉም፤ ግብጻውያንም፥ “እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ረድቶ እኛን እየተዋጋን ነው፤ ስለዚህ ከፊታቸው እንሽሽ!” ተባባሉ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) የሰረገሎቹንም መንኰራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፥ “እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ” አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) የሰረገሎቹንም መንኮራኵር አሰረ፤ ወደ ጭንቅም አገባቸው፤ ግብፃውያንም፦ “እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ይዋጋላቸዋልና ከእስራኤል ፊት እንሽሽ፤” አሉ። |
እንዲህም ሆነ፦ ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ ዓይናቸውም እያየ ብዙ ውድቀት ሆነ፥ ይህ ሥራ በአምላካችን እንደ ተከናወነ አወቁ።
በፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩ መካከል በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ አሳዳጆቻቸውን ግን በኃይለኛ ውኃ እንደሚጣል ድንጋይ ወደ ጥልቁ ጣልካቸው።
እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ፥ እርሱም ያሳድዳቸዋል፤ በፈርዖንና በሠራዊቱም ሁሉ ላይ ክብር አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ።
ጌታም እንዲህ ይለኛልና፦ አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሣ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንደዚሁም የሠራዊት ጌታ በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ለመዋጋት ይወርዳል።
ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ፦ መድረኮቹ እስኪናወጡ ድረስ ጉልላቶቹን ምታ፥ በሰዎቹም ራስ ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም።
ጌታም ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባራቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ።