ኢዮብ 20 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)1 ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “እንድመልስ ሐሳቤ ይገፋፋኝል፥ ስለዚህም ውስጤ መታገሥ አቅቶታል። 3 የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥ የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል። 4 ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥ 5 የክፉ ሰዎች ፉከራ አጭር መሆኑን አምላክን የሚክዱ ደስታቸው ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን? 6 ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥ ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥ 7 እንደ ፋንድያ ለዘለዓለም ይጠፋል፥ ያዩትም፦ ወዴት ነው ያለው? ይላሉ። 8 እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፥ እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል። 9 ያየችውም ዐይን ዳግመኛ አታየውም፥ ለስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ ይሰወራል። 10 ልጆቹ ድሆቹን ይክሳሉ፥ በገዛ እጆቹ ሀብቱን ይመልሳል። 11 አጥንቶቹ በወጣት ኃይል ተሞልተው ነበር፥ ነገር ግን አሁን ያ የወጣትነት ኃይሉ ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።” 12 “ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥ ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥ 13 ቢጠብቀውም ባይተወውም፥ በጉሮሮውም ቢይዘው፥ 14 መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፥ እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል። 15 የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፥ እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል። 16 የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፥ የእባብም ምላስ ይገድለዋል። 17 ወንዞቹን አይመለከትም፥ የማሩንና የቅቤውን ጅረት አያይም። 18 የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፥ እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም። 19 ድሀውን ረግጦአል፥ ትቶታልም፥ ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል።” 20 “ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና የወደደው ነገር አላዳነውም። 21 እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፥ ስለዚህ በረከቱም አይጸናም። 22 በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፥ የጉስቁልናም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች። 23 ሆዱን ሳያጠግብ እግዚአብሔር የቁጣውን ትኩሳት ይሰድድበታል፥ በምግብ መልክም ያዘንብበታል። 24 ከብረት መሣሪያም ቢሸሽ፥ የናስ ቀስት ይወጋዋል። 25 እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፥ ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፥ ፍርሃትም ይወድቅበታል። 26 ለከበሩ ዕቃዎቹ ጨለማ ተዘጋጅቶአል፥ በሰው እፍ ያልተባለች እሳት ትበላዋለች፥ በድንኳኑ ውስጥ የቀረውም ይጋያል። 27 ሰማይ በደሉን ይገልጥበታል፥ ምድርም ትነሣበታለች። 28 የቤቱም ንብረት ይሰናበታል፥ በቁጣው ቀን በጐርፍ ተጠራርጎ ይወሰዳል። 29 ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥ ከአምላክ የተመደበለት ርስቱ ይህ ነው።” |