Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ነህምያ 6 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የጠላቶች ሴራ መክሸፍ

1 እንዲህም ሆነ ምንም እንኳ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን ባልገጥምም ቅጥሩን እንደሠራሁ፥ አንድም የፈረሰ እንዳልቀረ ሰንባላጥ፥ ጦቢያና ዓረባዊው ጌሼም የቀሩትም ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ፥

2 ሰንባላጥና ጌሼም እንዲህ ብለው ላኩብኝ፦ “ናና በኦኖ ሜዳ ባሉት መንደሮች እንገናኝ፤” ነገር ግን ክፉ ሊያደርሱብኝ አቅደው ነበር።

3 እኔም እንዲህ ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው፦ “ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ መውረድም አልችልም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ሥራው ለምን ይቆማል?”

4 ይህንኑ ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም ይህንኑ ቃል መለስኩላቸው።

5 ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ የተከፈተ ደብዳቤ በእጁ አስይዞ ይህንኑ ቃል በአገልጋዩ ለአምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤

6 በውስጡ የተጻፈውም እንዲህ የሚል ነበር፦ “አንተና አይሁድ ልታምጹ እንዳቀዳችሁ፥ ለዚህም ቅጥሩን እንደሠራህ፥ ንጉሣቸውም ልትሆን እንደምትፈልግ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል ጌሼምም ብሎታል።

7 ‘ንጉሥ በይሁዳ አለ’ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም እንዲናገሩ ነቢያትን ሾመሃል፤ አሁንም ይህን ነገር በንጉሡ ዘንድ ይሰማል፤ ስለዚህ መጥተህ በአንድነት እንመካከር።”

8 እኔም እንዲህ ብዬ ላክሁበት፦ “አንተ ከምትለው ነገር አንድም አልተደረገም፥ አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋልና”

9 ሁሉም እንዲህ እያሉ አስፈራሩን፦ “ከሥራው እጃቸውን ያላላሉ፥ አይሠራምም” አሁንም እጄን አበርታ።

10 እኔም ወደ ሜሔጣብኤል ልጅ፥ ወደ ዴላያ ልጅ፥ ወደ ሼማዕያ ቤት ሄድሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና፦ “በእግዚአብሔር ቤት፥ በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ፥ የመቅደሱንም በሮች እንዝጋ፤ ሊገድሉህ ይመጣሉና፥ በሌሊት ሊገድሉህ ይመጣሉና” አለ።

11 እኔም፦ “እንደ እኔ ያለ ሰው ይሸሻልን? እንደ እኔ ያለ ነፍሱን ሊያድን ወደ መቅደስ የገባ ማን አለ? አልገባም” አልሁ።

12 እነሆ እግዚአብሔር እንዳልላከው አወቅሁ፥ በእኔ ላይ ትንቢት የተናገረው ጦቢያና ሰንባላጥ ገዝተውት ስለ ነበረ ነው።

13 ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ።

14 አምላኬ ሆይ፥ ጦቢያን፥ ሰንባላጥን ስለዚህ ሥራቸው ደግሞም ሊያስፈራሩኝ ነቢያቱን ኖዓድያና የተቀሩት ነቢያትን አስብ።


የቅጥሩ መጠናቀቅ

15 ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጠናቀቀ።

16 እንዲህም ሆነ፦ ጠላቶቻችን ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ ዓይናቸውም እያየ ብዙ ውድቀት ሆነ፥ ይህ ሥራ በአምላካችን እንደ ተከናወነ አወቁ።

17 ደግሞም በእነዚያ ቀኖች የይሁዳ መኳንንቶች ብዙ ደብዳቤዎቻቸውን ወደ ጦቢያ ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር።

18 በይሁዳ ለእርሱ የማሉለት ብዙ ሰዎች ነበሩና፤ የአራሕ ልጅ የሼካንያ አማች ነበረና፥ ልጁ ይሆሐናንም የቤራክያን ልጅ የሜሹላምን ሴት ልጅ አግብቷልና።

19 በተጨማሪም መልካም ሥራውን በፊቴ ይናገሩ ነበር፥ እኔ ያልሁትንም ለእርሱ ይነግሩት ነበር፤ ጦቢያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos