Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢዮብ 27 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)

1 ኢዮብም ምሳሌውን ቀጠለ፥ እንዲህም አለ፦

2 “ፍርዴን ያስቀረ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም ያስመረራት ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን!

3 እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥

4 ከንፈሬ ኃጢአትን አይናገርም፥ አንደበቴም ሽንገላን አያወጣም።

5 እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፥ እስክሞት ድረስ ንጹሕነቴን ከእኔ አላርቅም።

6 በጽድቄ እጸናለሁ እርሱንም አልተውም፥ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱም እንኳን ኅሊናዬ አይወቅሰኝም።”

7 “ጠላቴ እንደ በደለኛ፥ በእኔ ላይም የሚነሣ እንደ ኃጢአተኛ ይሁን።

8 እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በወሰደ ጊዜ፥ አምላክን የካደ ሰው ተስፋው ምንድነው?

9 በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን?

10 ሁሉንስ በሚችል አምላክ ደስ ይለዋልን? እግዚአብሔርንስ ሁልጊዜ ይጠራልን?

11 እኔ ስለ እግዚአብሔር ሥራዎች አስተምራችኋለሁ፥ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውን አልሸሽግም።

12 እነሆ፥ ሁላችሁም አይታችኋል፥ ታዲያ ለምን በከንቱ ትባክናላችሁ?”

13 “እነሆ የበደለኛ እድል ፈንታ ከእግዚአብሔር ዘንድ፥ ግፈኛም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበላት ርስት ይህችው፥

14 ልጆቹ ቢበዙ በሰይፍ ይሞታሉ፥ ዘሩም በቂ እንጀራ ከቶ አያገኝም።

15 ለእርሱ የተረፉትም በቸነፈር ይቀበራሉ፥ መበለቶቻቸውም አያለቅሱላቸውም።

16 እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢከምር፥ ልብስንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥

17 እርሱ ያዘጋጀው ይሆናል፥ ነገር ግን ጻድቅ ይለብሰዋል፥ ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል።

18 የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር፥ ጠባቂም እንደሚሠራው ጎጆ ነው።

19 ባለ ጠጋ ሆኖ ይተኛል፥ ነገር ግን ለመጨረሻ ጊዜ ነው፥ ዓይኑን ሲከፍት፥ እርሱም የለም።

20 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ታገኘዋለች፥ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች።

21 የምሥራቅ ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ይሄዳል፥ ከቦታውም ይጠርገዋል።

22 ነፋሱ ይጥልበታል፥ አይራራለትም፥ እርሱ ግን ከእጁ ፈጥኖ ለመሸሽ ይታገላል።

23 ነፋሱ ያጨበጭብበታል፥ ከስፍራውም በፉጨት ያስወጣዋል።”

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos