ሉቃስ 24:44 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እርሱም፥ “በሙሴ ኦሪት፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ እንዳለው፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የነገርኋችሁ ነገሬ ይህ ነው” አላቸው። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እርሱም፣ “ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል’ ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከዚያም “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙርም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም ይገባዋል ብዬ የነገርኋችሁ ቃል ይህ ነው፤” አላቸው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢየሱስም፥ “ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ለሙሴ በተሰጠው ሕግ፥ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ መፈጸም አለበት ብዬ የነገርኳችሁ ቃል ይህ ነው” አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እርሱም፦ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው። |
በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኰናውን ትነድፋለህ።”
መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ምስፍናም ከአብራኩ፥ ለእርሱ የሚጠብቀውን እስኪያገኝ ድረስ፤ የአሕዛብ ተስፋቸው እርሱ ነውና፤
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ ዋጋው ብዙ የሆነውን፥ የተመረጠውን፥ የከበረውንና መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ አኖራለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም።
ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።
ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፤
“እነሆ ለዳዊት የጽድቅ ቍጥቋጥ የማስነሣበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር፤ ንጉሥ ይነግሣል፤ ያስባል፤ በምድርም ፍርድንና ጽድቅን ያደርጋል።
“እነሆ ስለ እስራኤል ቤትና ስለ ይሁዳ ቤት የሰጠሁትን መልካም የተስፋ ቃል የምፈጽምበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።
“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከረዥሙ ዝግባ ጫፍ ላይ ቀንበጥን ወስጄ አኖረዋለሁ፤ ከጫፎቹም አንዱን ቀንበጥ እቀነጥበዋለሁ፤ በረዥምና በታላቅ ተራራም ላይ እተክለዋለሁ።
ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመልሰው አምላካቸውን እግዚአብሔርንና ንጉሣቸውን ዳዊትን ይፈልጋሉ፤ በኋለኛውም ዘመን እግዚአብሔርንና ቸርነቱን ያስቡታል።
“በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ቤት አነሣለሁ፤ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤
በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፣ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፣ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኅዘን ያዝኑለታል።
ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፣ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ።
በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፣ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፣ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል።
አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፣ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፣ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፣ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫንይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።
እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የናስ እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ እባቡም ሰውን ቢነድፍ የተነደፈው ሁሉ ይመልከተው፤ ይድናልም” አለው።
ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከባለ ደሙ እጅ ያድኑታል፤ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛው ከተማ ይመልሱታል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል።
ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።
“ለሰው ልጅ ብዙ መከራ ያጸኑበት ዘንድ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች፥ ጻፎችም ይፈትኑት ዘንድ፥ ይገድሉትም ዘንድ፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ አለው” አላቸው።
መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱ የዘለዓለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤ እነርሱም የእኔ ምስክሮች ናቸው።
በሁለተኛው መዝሙር፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ እንዳለ ኢየሱስን አስነሥቶ ተስፋውን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል።
ለእስራኤልም ልጆች፦ ‘እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋልና እርሱን ስሙት’ ያላቸው ይህ ሙሴ ነው።
ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።
የሳሌም ንጉሥ፥ የልዑል እግዚአብሔርም ካህን የሆነ፥ ይህ መልከ ጼዴቅ፥ አብርሃም ነገሥታትን ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው።
ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።
በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር።
ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም “እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና፤” አለኝ።