ኢሳይያስ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለንጉሡ ለአካዝ የመጣ መልእክት 1 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የአራም ንጉሥ ረአሶን፥ የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ሊይዙአትም አልቻሉም። 2 ለዳዊት ቤትም፥ “አራም ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል” የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ ተናወጠ። 3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው፥ “አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው መታጠቢያ ቦታ ውጡ፤ 4 እንዲህም በለው፥ “ተጠበቅ፥ ዝምም በል፤ አትፍራ፤ ከእነዚህ ከሚጤሱ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ የተነሣ ልብህ አይደንግጥ፤ ከተቈጣሁ በኋላ ይቅር እላለሁና። 5 የአራም ልጅና የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ፦ ክፉ ምክርን ተማከሩብህ እንዲህ ብለው፦ 6 ወደ ይሁዳ እንውጣና እንነጋገራቸው፤ ወደ እኛም እንመልሳቸው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባቸው፤” 7 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም። 8 የአራም ራስ ደማስቆ ነው፤ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ የኤፍሬም መንግሥት ከሕዝብ ይጠፋል፤ 9 የኤፍሬምም ራስ ሳምሮን ነው፤ የሳምሮንም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ነው። ባታምኑ አትጸኑም።” የአማኑኤል የልደቱ ትንቢት 10 እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 11 “ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለአንተ ለምን።” 12 አካዝም፥ “አልለምንም፤ አምላኬ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። 13 እርሱም አለ፥ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? እግዚአብሔርን ታደክማላችሁ፤ 14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። 15 ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሳያውቅ ቅቤና ማር ይበላል። 16 ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት፥ መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ፥ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ሀገር ባድማ ትሆናለች። 17 እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።” 18 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብፅ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝንብ፥ በአሦርም ሀገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል። 19 ይመጡማል፤ እነርሱም ሁሉ በሸለቆ፥ በመንደሮች፥ በምድር ጕድጓድ፥ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በጫካ ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ። 20 በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ ባመጣው ታላቅ ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይላጫል። 21 በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው ከላሞቹ አንዲት ጊደርንና ሁለት በጎችን ያሳድጋል፤ የአንዲት በግ ወተትም ሁለት ሰዎችን ያጠግባል። 22 ወተትም ይበዛል፤ በሀገሪቱ መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል። 23 በዚያም ወራት እንዲህ ይሆናል፤ ወይን በሀገሩ ሁሉ የበጀ ይሆናል፤ የአንድ ሺህ የወይን ዳስ ዋጋ አንድ ሺህ የብር ሰቅል ይሆናል። ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ምድር ሁሉ ትጠፋለች፤ እሾህንና ኵርንችትንም ትሞላለች፤ ፍርሀትም ይመጣል። 24 በፍላጻና በቀስት ይገቡባታል፤ ምድሪቱ ሁሉ ትጠፋለችና፥ እሾህንና ኵርንችትንም ትሞላለችና። 25 በሚታረሰውም ተራራ ሁሉ ላይ ፍርሀት ይመጣል፤ የበጎች መሰማርያ ይሆናል፤ በሬዎችም ይረግጡታል፤ እሾህና ኵርንችትም ያጠፋዋል። |