ሮሜ 15:16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህም ጸጋ የተሰጠኝ የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለአሕዛብ በማብሠር እንደ ካህን ሆኜ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ስለዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ አገለግላለሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እንድሆን ነው፥ ይህም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በአሕዛብ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን አገለግል ዘንድ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌልም እገዛ ዘንድ፥ በእኔ ትምህርት አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተወደደና የተመረጠ መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ። |
የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል ለማስተማር ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልኩትን የማገልገል ግዴታ ከፈጸምኩ ለሕይወቴ ዋጋ አልሰጠውም፤ ለነፍሴም አልሳሳለትም።
ጌታም ሐናንያን እንዲህ አለው፦ “እርሱ ስሜን ለአረማውያን፥ ለነገሥታትና ለእስራኤል ሰዎች የሚያሳውቅ፥ የእኔ ምርጥ መሣሪያ ስለ ሆነ ወደ እርሱ ሂድ፤
እንዲሁም በታላላቅ ተአምራትና በድንቅ ሥራዎች፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ከኢየሩሳሌምና ከአካባቢዋ ጀምሮ እስከ እልዋሪቆን ድረስ የክርስቶስን ወንጌል አስተምሬአለሁ።
ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? እነርሱ እናንተ እንድታምኑ ያደረጉአችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ እያንዳንዳቸው የሚያገለግሉትም ጌታ ለያንዳንዳቸው በመደበላቸው ሥራ ነው፤
እንግዲህ ሰው ሁሉ እኛን የክርስቶስ አገልጋዮች እንደ ሆንን የእግዚአብሔርንም ምሥጢር የመግለጥ ኀላፊነት የተሰጠን ባለ ዐደራዎች እንደ ሆንን አድርጎ ሊቈጥረን ይገባል።
ሰውነታችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁትና በውስጣችሁም የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ መሆኑን ታውቁ የለምን? እንግዲህ እናንተ የእግዚአብሔር ናችሁ እንጂ የራሳችሁ አይደላችሁም።
እነርሱ የክርስቶስ አገልጋዮች ናቸውን? እኔ ከእነርሱ ይበልጥ የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ፤ ይህንንም ስል እንደ እብድ ሆኜ ነው የምናገረው፤ ከእነርሱ ይበልጥ ብዙ ጊዜ በሥራ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ታስሬአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ተገርፌአለሁ፤ ብዙ ጊዜ ለሞት አደጋ ደርሼአለሁ፤
እግዚአብሔር ሰዎችን በእኛ አማካይነት ስለሚጠራ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ ስለዚህ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!” ብለን በክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን።
እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁና በእናንተ ዘንድ ተአምራትን የሚያደርገው ሕግን በመፈጸማችሁ ነውን? ወይስ የምሥራቹን ቃል ሰምታችሁ በማመናችሁ ነው?
ክርስቶስ እንደ ወደደንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም መዓዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ኑሩ።
ለእግዚአብሔር በእምነት በምታቀርቡት መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ የእኔም ሕይወት ተጨማሪ መሥዋዕት ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ደስ ይለኛል፤ እናንተም የደስታዬ ተካፋዮች ትሆናላችሁ።
የሚያስፈልገኝንና ከሚያስፈልገኝም በላይ የላካችሁልኝን ስጦታ ከኤጳፍሮዲቱስ እጅ ተቀብዬአለሁ፤ ይህም የእናንተ ስጦታ በመልካም መዓዛ እንደ ተሞላ መሥዋዕት እግዚአብሔር የሚቀበለውና ደስ የሚሰኝበት ነው።
እናንተ እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ በነበርንበት ጊዜ መከራና ስድብ ደርሶብናል፤ ነገር ግን ታላቅ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ወንጌሉን ለእናንተ እንድናስተምር አምላካችን ድፍረትን ሰጥቶናል።
ወንድሞች ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር።
ራሱ የሰላም አምላክ በሁሉ ነገር ይቀድሳችሁ፤ መንፈሳችሁ፥ ነፍሳችሁ፥ አካላችሁ በሙሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጣበት ቀን ያለ ነቀፋ ተጠብቆ ይኑር።
እውነተኛው ትምህርት ግን የሚገኘው ስለተመሰገነው እግዚአብሔር ከሚያበሥረው ክቡር ወንጌል ነው፤ ይህም ወንጌል ለእኔ በዐደራ የተሰጠኝ ነው።
እኔም እምነትንና እውነትን ለማብሠር ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ወደ አሕዛብ የተላክሁት በዚህ ምክንያት ነው፤ ይህንንም ስል እውነት እናገራለሁ እንጂ አልዋሽም።
እነዚህ ነቢያት ያገለግሉ የነበሩት እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳልነበረ ተገልጦላቸዋል፤ ያገለገሉአችሁም ከሰማይ በተላከው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት አሁን ወንጌልን ያበሠሩአችሁ ሰዎች የነገሩአችሁን በመግለጥ ነው፤ ይህን ነገር መላእክት እንኳ ለማየት ይመኙት ነበር።
ወደ ጌታ ኢየሱስ የምትቀርቡትም እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ሆናችሁ ለመታነጽ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ቅዱሳን ካህናት ትሆናላችሁ።