2 ቆሮንቶስ 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየክርስቲያኖች ልግሥና 1 ወንድሞች ሆይ! እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያን የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንወዳለን። 2 እነርሱ በብዙ መከራ ተፈትነዋል፤ ይሁን እንጂ ደስታቸው ታላቅ ነበር፤ በጣም ድኾች ቢሆኑም እንኳ ከፍ ያለ ልግሥና አድርገዋል። 3 የሚቻላቸውን ያኽልና ከሚቻላቸውም በላይ በፈቃደኛነት እንደ ሰጡ እኔ እመሰክርላቸዋለሁ፤ 4 በይሁዳ ያሉትን ክርስቲያኖች የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸውም አጥብቀው ለመኑን፤ 5 እነርሱ ያደረጉት እኛ ከጠበቅነው በላይ ነው፤ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥሎም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጥተዋል። 6 ይህን ሥራ አስቀድሞ የጀመረው ቲቶ ስለ ነበረ አሁንም ይህንኑ የልግሥና ሥራችሁን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርስ እርሱኑ ለምነነዋል። 7 እናንተ በእምነት፥ በንግግር፥ በዕውቀት፥ በትጋት፥ ለእኛም ባላችሁ ፍቅር በሁሉ ነገር ትበልጣላችሁ፤ በዚህ በልግሥና ሥራም እንድትበልጡ ይሁን። 8 ታዲያ፥ ይህን የምላችሁ በማዘዝ አይደለም፤ ነገር ግን የሌሎችን የመስጠት ትጋት ከእናንተ ትጋት ጋር በማወዳደር የእናንተን ፍቅር እውነተኛነት ለማረጋገጥ ብዬ ነው። 9 እናንተ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁ፤ እርሱ ምንም እንኳ ሀብታም ቢሆን በእርሱ ድኻ መሆን እናንተ ሀብታሞች እንድትሆኑ ስለ እናንተ ብሎ ድኻ ሆነ። 10 በዚህ ጉዳይ ለእናንተ መልካም መስሎ የታየኝን ምክር እሰጣችኋለሁ፤ ባለፈው ዓመት ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ይህን ለማድረግ በመጀመሪያ የፈለጋችሁት እናንተ ነበራችሁ። 11 ስለዚህ የመስጠት ፈቃደኛነታችሁ አሳብ በሥራ ላይ ውሎ ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ባላችሁ መጠን ያንን ያሰባችሁትን አሁን አድርጉ። 12 ለመስጠት መልካም ፈቃድ ካለ የሰው ልግሥና ተቀባይነት የሚያገኘው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለም። 13 ይህንንም ስል ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ እንጂ እናንተ በመስጠት ስትቸገሩ ሌሎች እንዲያርፉ ብዬ አይደለም። 14 እናንተ በምትቸገሩበት ጊዜ የእነርሱ ሀብት ለእናንተ ችግር እንዲውል አሁን የእናንተ ሀብት ለእነርሱ ችግር ይዋል፤ በዚህ ዐይነት በመካከላችሁ እኩልነት ይኖራል። 15 ይህም፦ “ብዙ የሰበሰበ አልተረፈለትም፤ ትንሽ የሰበሰበም አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ቲቶና ጓደኞቹ 16 እኔ ለእናንተ የማስበውን ያኽል ቲቶም ለእናንተ ከልቡ እንዲያስብ ያደረገ አምላክ ይመስገን። 17 ቲቶ ወደ እናንተ የሚመጣው በራሱ ፈቃድ ተነሣሥቶ በደስታ ነው እንጂ እኛ ስለ ለመንነው ብቻ አይደለም። 18 በወንጌል ስብከቱ በአብያተ ክርስቲያን ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ከእርሱ ጋር እንልካለን። 19 ከዚህም በላይ ይህ ወንድም እኛ ይህን በጎ ሥራ ለጌታ ክብር ስንፈጽምና ለማገልገል ያለንንም መልካም ፈቃድ ስንገልጥ አብሮን በመሄድ የሥራ ተካፋያችን እንዲሆን በአብያተ ክርስቲያን የተመረጠ ነው። 20 ይህን በልግሥና የተሰጠውን ገንዘብ ስናስተዳድር ምንም ዐይነት ነቀፌታ እንዳይደርስብን እንጠነቀቃለን። 21 ዓላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው። 22 ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉህ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከነቲቶ ጋር የላክነውም በዚሁ ምክንያት ነው፤ እርሱ በእናንተ ላይ ያለው እምነት ትልቅ ስለ ሆነ አሁን በዚህ ሥራ ለመርዳት ያለው ትጋት ከምንጊዜውም የበለጠ ነው። 23 ስለ ቲቶ ማወቅ ቢያስፈልግ እናንተን ለመርዳት አብሮኝ የሚሠራ የሥራ ጓደኛዬ ነው፤ ከእርሱ ጋር ስለሚመጡት ስለ ሌሎች ወንድሞች የሆነ እንደ ሆነ እነርሱ የአብያተ ክርስቲያን ተወካዮች ለክርስቶስ ክብር የቆሙ ናቸው። 24 ስለዚህ ፍቅራችሁን ግለጡላቸው፤ በዚህ ዐይነት ፍቅራችንና በእናንተ ላይ ያለን ትምክሕት ከንቱ አለመሆኑን ለአብያተ ክርስቲያን ሁሉ ታሳያላችሁ። |