ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእግዚአብሔር ጠላት ትዕቢተኛው ጺሩጻይዳን የሐሰት ካህናትንና የጣዖታቱን አገልጋዮች ሾመ። 2 መሥዋዕት ይሠዉላቸው ነበር፤ ወይኑንም ያፈስሱላቸው ነበር። 3 እነርሱም የሚበሉና የሚጠጡ ይመስለው ነበር። 4 በየጧቱም ላሞችንና በጎችን፥ ፍየሎችንና ጊደሮችንም ይሰጣቸው ነበር፤ ማታና ጧትም መሥዋዕት ይሠዋ ነበር፤ ከዚያችም ከረከሰችው መሥዋዕት ይበላ ነበር። 5 ዳግመኛም ለጣዖታቱ ይሠዉ ዘንድ ሌሎች ሰዎችን ያነሣሷቸውና ግድ ይሏቸው ነበር እንጂ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አልነበረም። 6 የመቃቢስንም ልጆች ያማሩ እንደ ሆኑና ፈጣሪያቸው እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩት ባዩአቸው ጊዜ እንዲሠዉና ከረከሰችውም መሥዋዕት እንዲበሉ የጣዖታቱ ካህናት ያስትዋቸው ዘንድ ወደዱ፤ እነዚህ የተባረኩ የመቃቢስ ልጆች ግን እንቢ አሏቸው። 7 የአባታቸውን ትእዛዝ ይጠብቃሉና፥ በጎ ሥራንም በመሥራት ጸንተዋልና፥ እግዚአብሔርንም ፈጽመው ይፈሩታልና እነርሱን እሺ ማሰኘት ተሳናቸው። 8 ባሰሯቸውና በሰደቧቸው፥ በቀሟቸውም ጊዜ፥ 9 ለጣዖቶችም መስገድንና መሠዋትን እንቢ እንዳሉ ለንጉሡ ለጺሩጻይዳን ነገሩት። 10 ስለዚህም ንጉሡ ተቈጣ፤ አዘነም፤ ያመጧቸውም ዘንድ አዘዘ፤ አምጥተውም በፊቱ አቆሙአቸው፤ እርሱም “ለጣዖቶች ስገዱ፤ መሥዋዕትንም ሠዉ” አላቸው። 11 እነርሱም መልሰው እንዲህ አሉት፥ “እኛስ በዚህ ነገር አንመልስልህም፤ ለረከሱ ለጣዖቶችህም መሥዋዕትን አንሠዋም።” 12 በብዙ ሥራም አስፈራራቸው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር አምነው ልባቸውን አስጨክነዋልና አልቻላቸውም። 13 እሳትም አንድዶ ጨመራቸው፤ እነርሱም ነፍሳቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ። 14 ከሞቱ በኋላም ሕያዋን ሆነው፥ የተመዘዙ ሰይፎቻቸውን ይዘው በመንግሥቱ ዙፋን ተኝቶ ሳለ በሌሊት ታዩት፤ እርሱም ፈጽሞ ፈራ። 15 እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “ጌቶች እሺ በሉኝ፤ ምን ላድርግላችሁ? ያዘዛችሁኝን ሁሉ አደርግ ዘንድ ነፍሴን አትውሰዷት፤” ፈጽመውም አስፈሩት። 16 እነርሱም፥ “እግዚአብሔር ፈጣሪህ እንደ ሆነ አስብ” እያሉ የሚገባውን ሁሉ ነገሩት፤ “ከዚህም ትዕቢትህ የሚሽርህና ከአባትህ ከዲያብሎስ ጋራ ወደ ታች ወደ ገሃነም የሚያወርድህ አለ፤ በዚያም አንተን የበደልንህ በደል ሳይኖር፥ ፈጣሪያችን እግዚአብሔርንም እያመለክን ሳለን፥ እግዚአብሔርነቱንም በመፍራት እየሰገድንለት ሳለን በእሳት እንዳቃጠልኸን ፍዳህን ሁሉ ትጨርሳለህ። 17 እርሱ ሁሉን የፈጠረ ነውና፥ ሰማይንና ምድርን፥ ባሕሩንና በውስጧ ያለውንም ሁሉ፥ 18 ፀሐይንና ጨረቃንም፥ ከዋክብትንም፥ ፍጥረቱንም ሁሉ የፈጠረ እርሱ እግዚአብሔር ነውና። 19 “በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ሁሉን የሚችል እርሱ ነው፤ የሚሳነውም የለም። የሚገድልና የሚያድን፥ የሚገርፍና ይቅር የሚል እርሱ ነው። 20 ሰማይንና ምድርን የሚገዛ እርሱ ነውና ከእጁ የሚያመልጥ የለም። 21 ከአንተ ከወንጀለኛውና አባትህ ሰይጣን ልቡናቸውን ካሳወራቸው እንደ አንተ ከአሉ ከወንጀለኞች በቀር እርሱ ከፈጠረው ፍጥረት ከትእዛዙ የሚወጣ የለም፤ አንተና እነዚያ ጣዖታቶችህም እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለባት ወደ ገሃነም በአንድነት ትወርዳላችሁ። 22 በእኛ ክፉ ነገርን ታደርግ ዘንድ ይኸን ክፉ ሥራ ያስተማረህ መምህርህ ሰይጣን ነው እንጂ ይኸን የምታደርግ አንተ ብቻ አይደለህምና። 23 የፈጠረህ እግዚአብሔርንም አላሰብኸውም፤ ራስህንም እንደ ፈጣሪህ እንደ እግዚአብሔር ታደርጋለህ። 24 እግዚአብሔር እስኪያዋርድህ ድረስ በእጅህ ሥራና በጣዖቶችህ ትታበያለህ፤ በምድር ላይም ስለ ሠራኸው ኀጢአትህና በደልህ ሁሉ ይበቀልሃል።” |