መልአኩና ጦብያ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ1 ወደ ራጉኤልም ቤት ደረሱ፤ ሣራም ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው፤ እንዲሁ እነርሱም እርሷን ደስ አሰኙአት፤ ወደ ቤትም አስገባቻቸው። 2 ራጉኤልም ሚስቱ አድናን፥ “ይህ ልጅ ድንቅ ነው፤ ከዘመዶች ወገን የሆነ ጦቢትን ይመስለዋል” አላት። 3 ራጉኤልም፥ “ወንድሞቻችን! እናንተ ከወዴት ናችሁ?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ወደ ነነዌ ከተማረኩት ከንፍታሌም ልጆች ነን” አሉት። 4 ራጉኤልም፥ “ወንድሜ ጦቢትን ታውቁታላችሁን?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “እናውቀዋለን” አሉት። እርሱም፥ “በሕይወት አለን? ደኅና ነውን?” አላቸው። 5 እነርሱም፥ “አዎ ደኅና ነው” አሉት፤ ጦብያም፥ “አባቴ ነው” አለው። 6 ራጉኤልም ተነሥቶ ሳመው፤ አለቀሰም። 7 “አንተ የደግ ሰው ልጅ ነህ” ብሎ መረቀው፤ የጦቢትም ዐይኖች እንደ ጠፉ ነገረው። የጦቢትም ዐይኖች እንደ ጠፉ በሰማ ጊዜ አዝኖ አለቀሰ። 8 ሚስቱ አድናና ልጁ ሣራም አለቀሱ፤ በደስታም ተቀበሉዋቸው፤ በግ አርደውም፥ ማዕድ አቀረቡላቸው፤ እጅግም መሸ። ጦብያም አዛርያን፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ በጎዳና ያልኸኝን ነገር ተናገር፤ ነገሩም ይለቅ፥” አለው። 9 ራጉኤልም ጦብያ መልአኩን እንደሚያነጋግረው ሰምቶ ጦብያን አነጋገረው፦ እንዲህም አለው፥ “አንድ ጊዜ ብላ፤ ጠጣ፤ ደስም ይበልህ፤ 10 ልጄ ለአንተ ትገባለችና፥ አንተም ታገባታለህና። 11 እኔም እውነቱን እነግርሃለሁ፤ ይህችን ልጄን ለሰባት ወንዶች አጋባኋት፤ ወደ እርሷም እንደ ገቡ በሌሊት ይሞታሉ፤ ነገር ግን አንድ ጊዜ ደስ ይበልህ፤” ጦብያም፥ “ነገሩን ለኔ እስክትጨርሱልኝ ድረስ፥ ነገሬንም እስክታጸኑልኝ ድረስ በዚህ ምንም አልቀምስም” አለ። 12 ራጉኤልም አለው፥ “ከአሁን ጀምሮ እንደ ሥርዐቱ ውሰዳት፤ አንተ ወንድሟ ነህና፥ እርሷም እኅትህ ናትና፤ ይቅር ባይ እግዚአብሔርም የሚበጀውን ያከናውንላችሁ።” 13 ልጁ ሣራንም ጠራት፤ እጅዋንም ይዞ ሚስት ልትሆነው ለጦብያ ሰጣት፤ “እነሆ በሙሴ ሥርዐት ውሰዳት፤ ወደ አባትህም ቤት አግባት” ብሎ መረቃቸው። 14 ሚስቱ አድናንም ጠራት፤ ወረቀትም ወስዶ ጻፈና አተማት። 15 ከዚህም በኋላ ይበሉ ጀመሩ። 16 አድናንም ጠርቶ፥ “አንቺ እኅቴ ሌላ የጫጕላ ቤት አዘጋጂ፤ ወደዚያም አግቢያት” አላት። 17 እንዳላትም አደረገች፤ ወደዚያም አገባቻት፤ አለቀሰችም፤ የልጅዋንም እንባ ጠረገች። 18 “ስለዚች ኀዘንሽ ፋንታ የሰማይና የምድር ጌታ ደስታን እንደሚሰጥሽ እመኝ” አለቻት። |