ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ጦቢት 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)መልአኩና ጦብያ ወደ ጤግሮስ ወንዝ እንደ ደረሱና ዓሣ እንደ ያዙ 1 በመንገዳቸውም ሲሄዱ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ማታ ደረሱ፤ በዚያም አደሩ። 2 ያም ልጅ ሊታጠብ ወረደ፤ ከውኃውም ውስጥ ዓሣ ወጥቶ ተወረወረ፤ ያንም ልጅ ይውጠው ዘንድ ወደደ። 3 መልአኩም፥ “ያን ዓሣ ያዘው” አለው፤ ያም ልጅ ዓሣውን ያዘው፤ ወደ የብስም አወጣው። 4 ያም መልአክ፥ “ዓሣውን እረደው፤ ልቡንና ጉበቱን፥ ሐሞቱንም ያዝ፤ አጥብቀህም ጠብቅ” አለው። 5 ያም ልጅ መልአኩ እንዳዘዘው አደረገ፤ ዓሣውንም ጠብሰው በሉ፤ ሁለቱም ገሥግሠው ሄደው፥ ወደ በጣኔስ ደረሱ። 6 ያም ልጅ መልአኩን አለው፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ! የዚህ ዓሣ ልቡ፥ ጉበቱና ሐሞቱ ለምንድን ነው?” 7 መልአኩም አለው፥ “ልቡና ጉበቱ፦ የሚያሳምም ክፉ ጋኔን ያደረበት ቢኖር፥ ወይም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ቢኖር ያን ለዚያ ሰው በፊቱ ያጤሱለታል፤ ሴትም ብትሆን ያጤሱላታል፤ ከዚያም በኋላ አይታመሙም። 8 ሐሞቱን ግን በዐይኑ ላይ ብልዝ ያለበትን ሰው ይኩሉታል፤ እርሱም ይድናል።” 9 ወደ ራጊስም በቀረቡ ጊዜ፥ 10 መልአኩ አለው፥ “አንተ ወንድሜ! ዛሬ በራጉኤል ቤት እናድራለን፤ እርሱም ዘመድህ ነው፤ አንዲት ልጅም አለችው፤ ስሟም ሳራ ይባላል፤ ሚስት ትሆንህ ዘንድ እንዲሰጥህ ስለ እርስዋ እናገራለሁ፤ ለአንተ ውርሷ ይደርስሃልና። 11 ከዘመዶችዋም ወገን አንተ አለህ፤ ልጂቱም ደግና ልባም ናት። 12 አሁንም ስማኝ፤ ለአባትዋም እነግረዋለሁ፤ ከራጊስም በተመለስን ጊዜ የሠርግ በዓል እናደርጋለን፤ ራጉኤል፦ በሙሴ ሕግ መሠረት ለሌላ ሰው ይሰጣት ዘንድ አይወድድምና፥ ብትሞትም በወደደ ነበር፤ከሰው ሁሉ ይልቅ ውርሷ ላንተ ይደርስሃልና።” 13 ያም ልጅ መልአኩን አለው፥ “አንተ ወንድሜ አዛርያ! ያቺን ልጅ ለሰባት ወንዶች እንዳጋቧት እኔ ሰምቻለሁ፤ ሁሉም በሠርጉ ጊዜ ሞቱ። 14 አሁንም እኔ ላባቴ ብቸኛ ነኝ፤ ወደ እርሷም በገባሁ ጊዜ እንዳልሞት ፥ ያባቴንና የናቴንም ሕይወት በእኔ ምክንያት በጭንቅ ወደ መቃብር እንዳላወርድ እፈራለሁ፤ የሚቀብራቸውም ሌላ ልጅ የላቸውምና።” 15 ያም መልአክ አለው፥ “ከዘመዶችህ ሚስት ታገባ ዘንድ አባትህ ያዘዘህን ቃል አታስብምን? አሁንም አንተ ወንድሜ ስማኝ፤ የጋኔኑ ነገርስ አያሳዝንህ፤ በዚች ሌሊት ከዘመዶችህ ወገን እርሷ ሚስት ሆና ትሰጥሃለችና፤ 16 ወደ ጫጕላ ቤትም በገባህ ጊዜ የዕጣን ዕራሪ ውሰድ፤ ከዚህም ዓሣ ከጉበቱና ከልቡ ጨምረህ አጢስበት። 17 ጋኔኑም በሸተተው ጊዜ ይሸሻል፤ ለዘለዓለሙም አይመለስም። ወደ እርሷም በገባህ ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ጩኹ፤ እርሱም ያድናችኋል፤ ይቅርም ይላችኋል። እንግዲህ አትፍራ፤ ከጥንት ጀምሮ እርሷን አዘጋጅቶልሃልና፤ አንተም ታድናታለህ፤ እርሷም ካንተ ጋራ ትሄዳለች፤ ከእርሷም ልጆችን እንደምትወልድ እነግርሃለሁ፤” ጦብያም ይህን ሰምቶ አደነቀ፤ ልቡም ወደ እርሷ ተሳበ፤ ወደ ባጥናም ደረሱ። |