የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


መጽሐፈ ሲራክ 44 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 44

ለ. በታሪክ ውስጥ ለቀድሞ አባቶች የቀረበ ውዳሴ

1 ታላቅ ሰዎችን፥ አባቶቻችንን፥ እንደ ትውልዳቸው ቅደም ተከተል እናመስግናቸው።

2 ጌታ ክብርን በብዛት ፈጥሯል፤ ታላቅነቱንም ከጥንት ጀምሮ አሳይቷል።

3 አንዳንዶች ነገሥታት ሆኑ፥ በኃያልነታቸውም ገናኖች ነበሩ፥ ሌሎች ብልህ አማካሪዎች፥ ትንቢትም ተናጋሪዎች ነበሩ።

4 ሕዝቡን በምክሮቻቸው ይመሩ፥ የሕዝብን ፍላጐት የተረዱ፥ ጥበብን ያስተማሩ ነበሩ።

5 የሙዚቃ ስለቶችን የነደፉ፤ የውዳሴ ቅኔዎችንም የጻፉ ነበሩ።

6 ሃብታሞችና ኃያላንም ሆነው በሰላም በቤታቸው የሚኖሩ ነበሩ።

7 እኒህ ሁሉ በጊዜው በነበሩ ሰዎች ዘንድ፤ የተከበሩ የዘመናቸውም ፈርጥ ነበሩ።

8 አንዳንዶች ስማቸውን ትተው አልፈዋል፥ ውሳሴዎቻቸውም እስከ ዛሬ ይዘምራሉ።

9 ቀሪዎች ግን እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ያለመታሰቢያ ቀርተዋል፥ እንዳልነበሩም ሆነዋል፤ ከእነርሱም በኋላ ልጆቻቸው እንዲሁ ይሆናሉ።

10 ነገር ግን መልካም ተግባሮቻቸው ያልተዘነጉ ታላላቅ ሰዎችም አሉ።

11 በዘራቸም መልካም ውርስ፥ የሆኑትን ልጆቻቸውን ያገኛሉ።

12 ዘሮቻቸው ትእዛዛቱን ያከብራሉ፤ የልጅ ልጆቻቸውም የእነርሱን ፈለግ ይከተላሉ።

13 ዘራቸው ለዘለዓለም ይኖራል፤ ዝናቸውም አይደበዝዝም።

14 ሥጋቸው በሰላም ተቀብሯል፤ ስማቸው ግን በሁሉም ትውልዶች ዘንድ ይታወሳል፥

15 ሕዝቡ ስለ ጥበባቸው ያወሳል፥ በጉባኤውም ፊት ይመሰገናሉ።

ሄኖክ

16 ሄኖክ ጌታን በማስደሰቱ ወደ ገነት ገባ፤ ለትውልዶቹ ሁሉ መለወጥም ምሳሌ ሆነ።

ኖኀ

17 ኖኀ እውነተኛ ሰው ነበር፤ ቁጣም በወረደ ጊዜ ወራሽ ሆነ። የጥፋት ውሃ በወረደም ጊዜ በእርሱ የተነሣ ምድር ዘር ቀረላት።

18 ከእርሱም ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳኖች ተደረጉ፤ እነርሱም ደግሞ ሕያዋን በጐርፍ እንደማይጠፉ አረጋገጡ።

አብርሃም

19 ታላቁ የሕዝቦች አባት አብርሃም በክብር የሚስተካከለው ከቶ አልነበረም።

20 የልዑል እግዚአብሔርን ሕጐች ጠብቋል፤ ከእርሱም ጋር ቃል ገብቷል። ቃል ኪዳኑን በሥጋው አረጋገጠ፤ በመከራም ጊዜ ታማኝነቱን አስመሰከረ።

21 እግዚአብሔርም በዘሩ አማካኝነት ሕዝቦችን ሊባርክ፥ እንደ ምድር ትቢያ ሊያበዛው፥ ዘሮቹን እንደ ከዋክብት ከፍ ከፍ ሊያደርግ፥ ምድርን ሊሰጣቸው፥ ከአንዱ ባሕር ወደ ሌላው፥ ከወንዙም እስከ ምድር ዳርቻዎች ሊያወርሳቸው ማለለት።

22 ሕዝቦችን እንደሚባርክ ለይስሐቅም አረጋግጦለታል።

23 ቃል ኪዳኑን በያዕቆብ ራስ ላይ አሳረፈ፤ ቡራኬውን ሰጠው፤ ምድርን ርስቱ እንድትሆን ፈቀደ፤ እርሱም ሸነሸናት፤ ለዐሥራ ሁለቱ ነገዶችም አከፋፈላቸው።