ሮሜ 8:10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ክርስቶስ ካደረባችሁ ግን ሰውነታችሁን ከኀጢአት ሥራ ለዩ፤ መንፈሳችሁንም ለጽድቅ ሥራ ሕያው አድርጉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ከሆነ ምንም እንኳ ሥጋችሁ በኃጢአት ምክንያት የሚሞት ቢሆን እግዚአብሔር ስላጸደቃችሁ መንፈሳችሁ ሕያው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። |
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አለው፥ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱም መጥተን በእርሱ ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን።
እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና።
እኔ በእነርሱ እኖራለሁ፤ አንተም በእኔ፤ በአንድ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ፤ አንተም እንደ ላክኸኝና እንደ ወደድኸኝ እኔም እነርሱን እንደ ወደድኋቸው።
እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም፤ እኔ የምሰጠው ውኃ በውስጡ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆንለታል እንጂ።”
ስለዚህም በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኀጢአት ወደ ዓለም ገባች፤ ስለዚችም ኀጢአት ሞት ገባ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኀጢአትን ስለ አደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ።
ኀጢአትም ሞትን እንደ አነገሠችው እንዲሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጸጋ ጽድቅን ለዘለዓለም ሕይወት ታነግሠዋለች።
ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው እርሱ አድሮባችሁ ባለ መንፈሱ ለሟች ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣታል።
መጽሐፍ እንዲሁ ብሎአልና የመጀመሪያው ሰው አዳም በነፍስ ሕያው ሆኖ ተፈጠረ፤ ሁለተኛው አዳም ግን ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው።
በሃይማኖት ጸንታችሁ እንደ ሆነ ራሳችሁን መርምሩ፤ እናንተ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር እንዳለ አታውቁምን? እንዲህ ካልሆነ ግን እናንተ የተናቃችሁ ናችሁ።
በሕይወት የምንኖር እኛም በሟች ሰውነታችን ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር ስለ ኢየሱስ ክስርቶስ ብለን ተላልፈን ለሞት እንሰጣለን።
ከክርስቶስ ጋርም ተሰቀልሁ፤ ሕይወቴም አለቀች፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሕይወት አለሁ፤ ዛሬም በሥጋዬ የምኖረውን ኑሮ የወደደኝን ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ የሰጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመን እኖራለሁ።
በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ፥ በከክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፤ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛል፤ ይበልጥብኛልም።
ዛሬ ግን እግዚአብሔር የዚህን ምክር የክብር ባለጸግነት በአሕዛብ ላይ እንዲገልጽላቸው ለፈቀደላቸው ለቅዱሳን ተገለጠላቸው፤ የምንከብርበት አለኝታችን በእናንተ አድሮ ያለ ክርስቶስ ነውና።
ስማቸው በሰማይ ወደ ተጻፈ ወደ ማኅበረ በኵርም፥ ሁሉን ወደሚገዛም ወደ እግዚአብሔር፥ ወደ ፍጹማን ጻድቃንም ነፍሳት፥
ከሰማይም እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ። “ይህንን ጻፍ፡ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው።” መንፈስም “አዎን! ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል፤” ይላል።