ፊልጵስዩስ 3 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለሚያበረታታ ትምህርት 1 አሁንም ወንድሞች ሆይ፥ በጌታችን ደስ ይበላችሁ፤ እኔም ስጽፍላችሁ ቸል አልልም፤ ያበረታችኋልና። 2 ከውሾች ተጠበቁ፤ ከክፉ አድራጊዎችም ተጠበቁ፤ ሥጋቸውን ብቻ በመቍረጥ ተገዝረናል ከሚሉም ተጠበቁ። 3 ግዙራንስ እግዚአብሔርን በመንፈስ የምናገለግለውና የምናመልከው እኛ ነን፤ እኛም በኢየሱስ ክርስቶስ እንመካለን እንጂ በሥጋችን የምንመካ አይደለም። 4 እኔም ግዝረት ሳለኝ በግዝረት አልመካም፤ በግዝረት መመካትን የሚያስብ ካለም እኔ እርሱን እበልጠዋለሁ። 5 በስምንተኛው ቀን የተገዘርሁ፥ ከእስራኤል ሕዝብ ከብንያም ነገድ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ በኦሪትም ፈሪሳዊ ነበርሁ። 6 በኦሪት ጽድቅም ያለ ነውር ሆኜ በቅንዐት ምእመናንን አሳድድ ነበር። 7 ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ያን ጥቅሜን ላጣው ወደድሁ። 8 ክርስቶስን አገለግለው ዘንድ፥ ሁሉን የተውሁለት፥ እንደ ጕድፍም ያደረግሁለት የጌታዬን የኢየሱስ ክርስቶስን ኀይልና ገናናነት ስለማውቅ ሁሉን እንደ ኢምንት ቈጠርሁት። 9 በእርሱም እጸና ዘንድ፥ ዛሬ የኦሪት ጽድቅ ሳይኖረኝ ክርስቶስን በማመን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጽድቅ አለኝ እንጂ። 10 በእርሱም ኢየሱስ ክርስቶስን አውቀዋለሁ፤ የመነሣቱንም ኀይል በሕማሙ እሳተፈዋለሁ፤ በሞቱም እመስለዋለሁ። 11 ይኸውም ሙታን በሚነሡ ጊዜ ምናልባት በዚህ አገኘው እንደ ሆነ ብዬ ነው። ዋጋን ስለ መጠባበቅ 12 ነገር ግን ይህን ፈጽሜ የተቀበልሁ አይደለም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እርሱ እኔን የመረጠበትን አገኝ ዘንድ እሮጣለሁ እንጂ። 13 ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግን ፍጻሜዬን ገና ያገኘሁ አይመስለኝም። 14 የኋላዬን እረሳለሁና፥ ወደ ፊቴም ፈጥኜ እገሠግሣለሁና፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን የጥሪ ዋጋ ለማግኘት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ። ስለ ፍጹማን ምእመናን 15 ፍጹማን የሆናችሁ ሁላችሁ ይህን አስቡ፤ ሌላ የምታስቡት ቢኖርም፥ እርሱን እግዚአብሔር ይገልጥላችኋል። 16 ነገር ግን በደረስንበት ሥራ በአንድነት እንበርታ። 17 ወንድሞች ሆይ፥ እኔን ምሰሉ፤ እንዲህ ባለ መንገድ የሚሄዱትንም እኛን ታዩ እንደ ነበረበት ጊዜ ተጠባበቋቸው። 18 ዘወትር እንደምነግራችሁ፥ ልዩ አካሄድ የሚሄዱ ብዙዎች አሉና፤ አሁንም እነርሱ የክርስቶስ የመስቀሉ ጠላቶች እንደ ሆኑ በግልጥ እያለቀስሁ እነግራችኋለሁ። 19 እነዚህም ፍጻሜያቸው ለጥፋት የሆነ፥ ሆዳቸውን የሚያመልኩ፥ ክብራቸውም ውርደት የሆነባቸው፥ ምድራዊዉንም የሚያስቡ ናቸው። 20 እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት፤ ከዚያም እርሱን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን። 21 እርሱም እንደ ከሃሊነቱ ረዳትነት መጠን የተዋረደውን ሥጋችንን የሚያድሰው፥ ክቡር ሥጋዉንም እንዲመስል የሚያደርገው፥ የሚያስመስለውም፥ ሁሉም የሚገዛለት ነው። |