ነህምያ 9:5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሌዋውያኑም ኢያሱና ቀድምኤል፥ እንዲህ አሉ፥ “ቆማችሁ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አምላካችንን እግዚአብሔርን አመስግኑ። የከበረ ስሙንም አመስግኑ፤ በበረከትና በምስጋናም ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አድርጉት።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ቀድምኤል፣ ባኒ፣ አሰበንያ፣ ሰራብያ፣ ሆዲያ፣ ሰበንያና ፈታያ፣ “ተነሥታችሁ ቁሙ፤ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የሚኖረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ወድሱ” አሉ። “ክቡር ስምህ የተመሰገነ ይሁን፤ ከምስጋና ሁሉና ከውዳሴም በላይ ከፍ ከፍ ይበል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ሌዋውያኑ ኢያሱ፥ ቃድምኤል፥ ባኒ፥ ሐሻብንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሽባንያ፥ ፕታሕያ እንዲህ አሉ፦ “ቁሙ፥ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ጌታ አምላካችሁን ባርኩ። ከበረከትና ከምስጋና ሁሉ በላይ ከፍ ያለው የክብርህን ስም ይባርኩ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኢያሱ፥ ቃድሚኤል፥ ባኒ፥ ሐሸባንያ፥ ሼሬብያ፥ ሆዲያ፥ ሸባንያና ፐታሕያ ተብለው የሚጠሩት ሌዋውያን፦ “ተነሥታችሁ በመቆም ዘለዓለማዊውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ከምስጋናና ከበረከት ሁሉ በላይ፥ ከፍ ከፍ ይበል! በሉ” አሉአቸው። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ፦ ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ፦ በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ። |
“በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ ለስምህ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ!
ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። ሕዝቡ ሁሉ አሜን ይበሉ፤ እግዚአብሔርንም ያመስግኑ።
አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኀይል፥ ክብርም፥ ድልና ጽንዕ የአንተ ነው፤ ነገሥታቱና ሕዝቡ ሁሉ በፊትህ ይደነግጣሉ።
ዳዊትም ጉባኤውን ሁሉ፥ “አምላካችን እግዚአብሔርን አመስግኑ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፥ በጕልበታቸውም ተንበርክከው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ደግሞም ለንጉሡ።
ሌዋውያንም፥ ከቀዓት ልጆችና ከቆሬ ልጆች የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ከፍ ባለ ታላቅ ድምፅ ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።
ደግሞ፥ “ቸር ነውና፥ ለእስራኤልም ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” እያሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ እርስ በርሳቸው ያስተዛዝሉ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቤት በተመሠረተ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩ በታላቅ ድምፅ ዘመሩ።
ሌዋውያኑም ኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ የሰራብያ ልጅ ሴኬንያ፥ የከናኒ ልጆችም በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ።
ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን፥ ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድርንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ ፈጥረሃል፤ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ።
እንዲህም አለ፥ “ከእናቴ ማኅፀን ራቁቴን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ የእግዚአብብሔር ስም የተባረከ ይሁን።”
እግዚአብሔር እርሱ አምላካችን እንደ ሆነ ዕወቁ፤ እርሱ ፈጠረን፥ እኛም አይደለንም፤ እኛስ ሕዝቡ የመሰማርያውም በጎች ነን።
አቤቱ፦ በአማልክት መካከል አንተን የሚመስል ማን ነው? በቅዱሳንም ዘንድ እንደ አንተ የከበረ ማን ነው? በምስጋና የተደነቅህ ነህ፤ ድንቅንም የምታደርግ ነህ፤
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ።
በጨለማ ውስጥ “ብርሃን ይብራ” ያለ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት የክብሩን ዕውቀት ብርሃን በልባችን አብርቶልናልና።
“በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ፥ ይህንም ክቡርና ምስጉን ስም እግዚአብሔር አምላክህን ትፈራ ዘንድ ባትሰማ፥
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኀይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።