መዝሙር 145 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር። ሃሌ ሉያ። 1 ነፍሴ እግዚአብሔርን ታመሰግነዋለች። 2 በሕይወቴ ሳለሁ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፤ በምኖርበት ዘመን መጠን ለአምላኬ እዘምራለሁ። 3 ማዳን በማይችሉ በአለቆችና በሰው ልጆች አትታመኑ። 4 ነፍሳቸው ትወጣለች፥ ወደ መሬትም ይመለሳሉ፤ ያንጊዜ ምክራቸው ሁሉ ይጠፋል። 5 የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ፥ መታመኛውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ብፁዕ ነው። 6 እርሱም ሰማይንና ምድርን ባሕርንም፥ በእነርሱ ውስጥ ያለውንም ሁሉ የፈጠረ፤ እውነትን ለዘለዓለም የሚጠብቅ፤ 7 ለተበደሉትም የሚፈርድላቸው፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታቸዋል፤ 8 እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣቸዋል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳቸዋል፤ 9 እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃቸዋል፤ ድሃ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላቸዋል፤ የኃጥኣንንም መንገድ ያጠፋል። 10 እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፥ አምላክሽ ለልጅ ልጅ ነው። |