መዝሙር 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት ጸሎት። 1 አቤቱ፥ ጽድቄን ስማኝ፥ ልመናዬንም አድምጠኝ፤ በተንኰለኛም ከንፈር ያልሆነውን ጸሎቴን አድምጠኝ፤ 2 ፍርዴ ከፊትህ ይወጣል፥ ዐይኖቼም ጽድቅህን አዩ። 3 በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፥ ፈተንኸኝ፥ ዐመፅም አልተገኘብኝም። 4 የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር፥ ስለ ከንፈሮችህ ቃል ጭንቅ የሆኑ መንገዶችን ጠበቅሁ። 5 ሰኰናዬ እንዳይናወጥ አረማመዴን በመንገድህ አጽና። 6 እግዚአብሔር ሰምቶኛልና እኔ ጮኽሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ቃሌንም ስማ። 7 ቀኝህን ከሚቃወሟት፥ የሚያምኑብህን የሚያድናቸውን ቸርነትህን ግለጠው። 8 እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ፤ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ፤ 9 ከሚያጐሳቍሉኝ ኃጥኣን ፊት፥ ጠላቶቼ ግን ነፍሴን ተመለከትዋት፤ 10 አንጀታቸውን ቋጠሩ፥ አፋቸውም ትዕቢትን ተናገረ። 11 አሁንም አባረሩኝ፤ ከበቡኝም፤ ዐይናቸውንም ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ። 12 እነርሱ ለንጥቂያ እንደሚሸምቅ አንበሳ፥ ተሰውሮም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ግልገል ተቀበሉኝ። 13 አቤቱ፥ ተነሥ፥ ደርሰህ አሰናክላቸው፤ ነፍሴንም ከጦር አድናት። 14 ሰይፍህ በእጅህ ጠላቶች ላይ ናት። አቤቱ፥ በምድር ካነሱ ሰዎች፥ በሕይወታቸው ከፋፍላቸው፥ ከሰወርኸው ሆዳቸው ጠገበች፤ ልጆቻቸው ጠገቡ። የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ተዉ። 15 እኔ ግን በጽድቅህ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን በማየትም እጠግባለሁ። |