ማቴዎስ 3:12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም መንሹ በእጁ ነው፤ ዐውድማውን ፈጽሞ ያጠራል፤ ስንዴውን በጐተራ ይከትታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መንሹ በእጁ ነው፤ አውድማውንም ያጠራል፤ ስንዴውን በጎተራ ይከተዋል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እርሱ መንሹ በእጁ ነው። በእርሱም አውድማውን ደኅና አድርጎ ያጠራል። ስንዴውን በጐተራ ይከተዋል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። |
ኀይላቸውም እንደ መቃ መስዬ፥ ሥራቸውም እንደ ጠለሸት ይሆናል፤ ኃጥአንና ዐማፅያንም አብረው ይቃጠላሉ፤ እሳቱንም የሚያጠፋላቸው ያጣሉ።”
ብዙዎች አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ናቸው፤ ከፏፏቴ ውስጥ በኀይል እንደሚወርድ እንደ ብዙ ውኃ ፈሳሽ ይጮኻሉ፤ ያጠፉታልም፤ እነርሱም ከሩቅ ይወርዳሉ፤ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ፥ በነፋስ ፊት ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው እንደ መንኰራኵር ትቢያም ይበተናሉ።
ስለ ጠቡ በእሳት አቃጥለው ዘንድ ቀርቃሃና ሣርን ማን በሰጠኝ! አሁንም እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ ዛሬ አደረገ፤ እነርሱ ተቃጥለዋልና።
መሬትንም የሚያርሱ በሬዎችና አህዮች በመንሽና በወንፊት የነጻውን ከገብስ ጋር የተቀላቀለውን ገፈራ ይበላሉ።
ስለዚህ ገለባ በእሳት ፍም እንደሚቃጠል፥ በነበልባልም እንደሚበላ፥ እንዲሁ የእነርሱ ሥር የበሰበሰ ይሆናል፤ አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ጥለዋልና፤ የእስራኤልም ቅዱስ የተናገረውን ቃል አቃልለዋልና።
ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸውም አይጠፋም፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ ምሳሌ ይሆናሉ።”
ሕዝቤንም ወደ ዳርቻ ፈጽሜ እበትናቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፤ ሕዝቤንም ስለ ኀጢአታቸው አጥፍቻቸዋለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም።
ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም ግንቦች ትበላለች፤ አትጠፋምም።
በዚያ ጊዜ ለዚህ ሕዝብና ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይሏቸዋል፦ በምድረ በዳ የሚያስት ጋኔን አለ፤ የሕዝቤ ሴት ልጅ መንገድም ለንጽሕና ወይም ለቅድስና አይደለም።
በባቢሎንም ላይ ተሳዳቢ ሰዎችን እሰድዳለሁ፤ እነርሱም ይሰድቧታል፤ ምድርዋንም ባዶ ያደርጋሉ፤ በመከራም ቀን በዙሪያዋ ይከብቡአታል።
እንግዲህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።”
ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋት እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፋስም ከዐውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከምድጃም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።
እነሆ አዝዛለሁ፤ እህልም በመንሽ እንደሚዘራ የእስራኤልን ቤት በአሕዛብ ሁሉ መካከል እዘራለሁ፤ ነገር ግን አንዲት ቅንጣት በምድር ላይ አትወድቅም።
እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፣ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፣ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን “እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ፤” እላለሁ’ አለ።”
ዮሐንስም መልሶ ሁሉንም እንዲህ አላቸው፥ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ግን የሚበልጠኝ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ልፈታለት የማይገባኝ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ፥ በእሳትም ያጠምቃችኋል።
መንሹ በእጁ ነው፤ የዐውድማውንም እህል ያጠራል፤ ስንዴውንም በጎተራው ይሰበስባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥላል።”
በእኔ ያለውን፥ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍም ሁሉ ያስወግደዋል፤ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ግን በብዙ እንዲያፈራ ያጠራዋል።